በምግብና በመድሃኒት እጥረት ለሚሰቃዩ ዜጎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ተፈናቃዮች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በምግብና በመድሃኒት እጥረት ለሚሰቃዩ ዜጎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ተፈናቃዮች ጠየቁ
ደሴ፣ መስከረም 4/2014 (ኢዜአ ) ''የአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሀይል በከፈተው ጦርነት በምግብና በመድሃኒት እጥረት ለሚሰቃዩ ዜጎች መንግስት ፣ ህዝብና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፈጥነው ሊደርሱላቸው ይገባል ሲሉ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የተጠለሉ ወገኖች ጠየቁ፡፡
ተፈናቃዮቹ ጥያቄውን ያቀረቡት ዛሬ በደሴ ከተማ ጎዳናዎች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው።
ሰልፈኞቹ ለአማራና አፋር ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ይደረግላቸው፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተጎጂዎችን ሊደግፉ ይገባል፤ የሚሉና መሰል መፈክሮችን አሰምተዋል።
ከወልድያ ከተማ የተፈናቀሉት ወይዘሮ አበበች ውበቱ እንደገለጹት የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሀይል ድንገት በከፈተው ጦርነት ወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ሲጋፈጡ ሴቶች ጫካ ለጫካ ተሹለክልከው ደሴ ከተማ ገብተዋል።
ወራሪው ሀይል ከባድ መሳሪያ ተጠቅሞ ከተማውን ሲቆጣጠር አዛውንቶች፣ አቅመ ደካሞችና ታማሚዎች መውጣት ስላልቻሉ ባሉበት መቅረታቸውን ተናግረዋል።
ወራሪው በየቤቱ እየዞረ ንጹሀንን ከመግደል ባለፈ ምግብና ቁሳቁስ በመዝረፉና በማውደም ግፍ መፈጸሙን አመልክተዋል ።
የስኳር፣ ደም ግፊትና ሌሎች ታማሚዎችም በቋሚነት የሚወስዱት መድሃኒት በማለቁ በመድሃኒት እጥረት የሚሞቱ ነዋሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በዚሁ ምክንያት አንዲት ዘመዳቸውና ጎረቤቶቻቸው ሰሞኑን መሞታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከሐራ ከተማ የተፈናቀሉ ወይዘሮ ቀመርያ ኑርዬ በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ሀይል በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈጽመው ግፍ ዘመን የማይሽረው ጥቁር ጠባሳ መሆኑን ተናግረዋል።
ወራሪው ከተማውን ሲቆጣጠር በሽሽት ላይ እያሉ በጫካ ውስጥ ብቻቸውን ወልደው እዛው የቀሩና አሁን ላይ በምግብ እጥረት ጡት ማጥባት አቅቷቸው ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የስኳርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒት ይወስዱ የነበሩ ሰዎችም በመድሃኒት እጥረት ስለመሞታቸው መርዶ የደረሳቸው መሆኑን አመልክተዋል።
"እኛን የደሴ ህዝብ እያበላን ቢሆንም የቤተሰቦቻችን ጉዳይ አስጨንቆናል" ሲሉ ችግሩን በአጽእኖት ገልጸዋል።
"ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ለአማራና አፋር ክልል ተፈናቃዮችና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ድጋፍ አለማድረጋቸው ትክክል አይደለም" ያሉት ደግሞ አቶ ፀሐይ ነጋሽ ናቸው፡፡
"እንደኛ እድሉን ሳያገኙ ከአካባቢያቸው መውጣት ያልቻሉ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ህዝብ በምግብና በመድሃኒት እጥረት እየሞቱ መሆኑ ያሳስበናል፤ ሁሉም ድምጽ ሊሆናቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
"እኛ ህብረተሰቡ በሚያቀርብልን የእለት ደራሽ ምግብ እንዲሁም ስንታመም የነጻ ህክምና እያገኘን ህይወታችንን እያስቀጠልን ነው" ያሉት አቶ ፀሐይ ባሉበት የቀሩ ወገኖቻቸው ስቃይ እያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፣ መንግስትና ህዝብ በምግብና መድሀኒት እጥረት እየተሰቃዩ ለሚገኙ ዜጎች ፈጥነው እንዲደርሱ ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል።