በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የሚለው ዘመቻ እየተካሄደ ነው

85

አዲስ አበባ መስከረም 4/2014 በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የሚለው ዘመቻ በርካታ ወጣቶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ በትናንትናው ዕለት ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና በርካታ ወጣቶች በተገኙበት በይፋ መጀመሩ ይታወሣል።

በዛሬው ዕለትም በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ይህ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተገኘበትም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዘመቻ በይፋ ተጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ መርሃ ግብር ወጣቶች ለነጩ ቤተ መንግስት የሚደርስ እና የኢትዮጵያን እውነታ የያዘ መልዕክት እና የአሸባሪውን ቡድን ሃገር የማፍረስ እኩይ ዓላማን የሚያጋልጥ ደብዳቤ በነጭ ፖስታ በማድረግ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሃላፊ እና የፓለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዱልሰመድ ሻሚል እንዳሉት፤ የአገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን አደጋ የተመለከተ እና የውጪ አገራትን ጣልቃ ገብነት መቃወም ዓላማ ያደረገ ነው።
በተለይ አሜሪካ የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ተግባር እንድትረዳ እና የኢትዮጵያን እውነታ እንድትገነዘብ ለማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ በክፍለ ከተማው ከ200 ሺ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙም ተገልጿል። 

መርሃ ግብሩም እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ ንቅናቄ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲደርስ ይሰራል መባሉን ኢዜአ በትናንትናው ዕለት በዘመቻው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መገለጹን መዘገቡ ይታወሣል። 

በዚህ ዘመቻ በአጠቃላይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም