የኢትዮ - ኬንያ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት ተጀመረ

70

አዲስ አበባ መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጲያና ኬንያ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት ዛሬ ጀምረዋል።

ኢትዮ - ኬንያ ለኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸው ተገልጿል፡፡

የሁለቱ አገራት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች አማካኝነት ዛሬ የተጀመረው ውይይት ለሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለውን የኢነርጂ መሰረተ ልማት ግንባታ ሂደትን ለማፋጠን በሚያስችሉና በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ታውቋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የኬንያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትር ሚስተር ቻርለስ ኬተር ከልዑካን ቡድኖቻቸው ጋር በመሆን ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሮቹ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት፤ ሁለቱ አገራት ለኃይል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰዋል።

ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመው የሁለቱ አገራት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሊያስተሳስር የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት ተገንብቶ አገልግሎት ሲጀመር ለሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ሚኒስትሮቹ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው የ412 ኪሎ ሜትር የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመርና የዲሲ ኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የሙከራና ፍተሻ ስራ ተከናውኖበታል፡፡

በተመሳሳይ በኬንያ በኩል መዘርጋት ካለበት 633 ኪሎ ሜትር ውስጥ 30 ኪሎ ሜትር ብቻ መቅረቱ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።

በመሆኑም ቀሪውን ግንባታ በቀጣይ አንድ ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኬንያ ኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትር ቻርለስ ኬተር አስታውቀዋል።

ዛሬ የተጀመረው የሁለትዮሽ ውይይት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ሲጠናቀቅ የሙከራ ስራ በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ለመምከርና ቀደም ሲል የተፈረመው የኃይል ሽያጭ ስምምነት ላይ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ ነው ተብሏል።

የአገራቱ ባለሙያዎች ስምምነቱን በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ሚኒስትሮቹ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

የሁለቱ አገራት የባለሙያዎች ቡድን ዝርዝር በሆኑ የስምምነትና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም