ድጋፋችን አሸባሪው ህወሃት የፈጸመው ወረራ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ይቀጥላል -- አቶ ርስቱ ይርዳው

104

ሠመራ ፤ መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) ድጋፋችን የጋራ ጠላታችን የሆነው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈጸመብን ወረራ በአስተማማኝ ሁኔታ እልባት መስጠት እስከሚችል ድረስ ይቀጥላል ሲሉ የደቡብ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

አቶ ርስቱ አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ላፈናቀላቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲውል 25 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 800 ኩንታል የዳቦ ዱቄት እና 8ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ዛሬ በሠመራ ከተማ በመገኘት ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።

በርክክቡ ስነ-ስርዓት ወቅት አቶ ርስቱ ፤ የአፋር ህዝብ ለዘመናት ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር ውድ የህይወት ዋጋ ሲከፋል ኖሯል፤ ይህም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ግመሎቻችንም ያውቁታል የሚለው ዘመን ተሻጋሪ ሀቅ የሚያረጋግጠው ነው ብለዋል። 

ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር ባልተመቻቸና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ ውድ ዋጋ እየከፈለ ላለው የአፋር ክልል ህዝብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎኑ መቆም ይኖርብናል ነው ያሉት።

ድጋፋችን የጋራ ጥላታችን የሆነው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈጸመብንን ወረራ በአስተማማኝ ሁኔታ እልባት መስጠት እስከሚችል ድረስ ይቀጥላል ሲሉ አቶ ርስቱ ይርዳው አስታውቀዋል።

የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት ትርጉም የሌለው ጦርነት በመክፈትና በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህዝቡን እያጭበረበረ አለፍም ሲል እያፈነ የሚስኪን ደሃ ትግራይን ህጻናት አስገድዶ በግፍ እያስጨረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አሁን ባለንበት ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ የሰብአዊነት ክብር የረከሰበት አስከፊ ክልል ትግራይ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

ቁሜለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብም የማይጠቅመው  የሽብር ቡድን ከመሰረቱ ነቅሎ ለመጣል ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተባብረን መስራትና በጋራ መቆም ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብና ሌሎችም ክልሎች እንዲሁም የተለያዩ አጋሮች ለተጎጂዎቹ እያደረጉ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍና አጋርነት የወደፊት ተስፋቸውን የሚያለመልም መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም