በሠራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የአሸባሪው ህወሃት ህልም ከንቱ የሆነበት የማይጠብሪ ግንባር

259

አዲስ አበባ መስከረም 3/2014(ኢዜአ) በሠራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የአሸባሪው ህወሃት ህልም ከንቱ የሆነበት የማይጠብሪ ግንባር

አሸባሪው ህወሃት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንሄዳለን” በሚሉ አፈ-ቀላጤዎች እየተመራ ይህን ውጥኑን ለማሳካት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ መፈጸሙ ይታወሳል።

ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሞፈርን ከመሬት አዋደው ህይወታቸውን የሚገፉ አርሶ አደሮችን ጨፍጭፏል፤ የእምነት ተቋማትን በከባድ መሳሪያ በመደብደበ አፍርሷል፤ የግለሰቦችን እና የመንግስት ንብረት ዘርፏል፤ መሰረተ ልማቶችንም አውድሟል።

ወትሮም ቢሆን “ከአገሬ በፊት እኔ ልሰዋ” በሚል የጀግነት ተጋድሎ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የአገሪቷ ጥግ ሆ ብለው በመነሳት የሽብር ቡድኑን ቅዥት እያከሸፉት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት የማይለያቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሎች ልዩ ሃይሎች እንዲሁም ሚኒሻዎች ደግሞ የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሃይሎች በየተሰማሩበት አውደ ውጊያ ድባቅ እየመቱት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የውቅን ተራራ ህያው ምስክር ነው።

አሸባሪው ህወሃት ራሱ የሰየማቸውና ያደራጃቸው “ሶስት ኮሮችና ዘጠኝ ክፍለጦሮች” በከሃዲው ጄኔራል ምግበይ እየተመሩ ወረራ ከፈጸሙት ከአስር ሺህ በላይ ታጣቂዎች በመያዝ በሰሜን ጎንደር በኩል አድርገው የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት አቅደው ተንቀሳቅሰዋል።

በማይጠብሪ ግንባር ውቅን ተራራ ላይ ሲደርሱ ግን ያልጠበቁት ጉዳይ ገጠማቸው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አቢይ አህመድ ከጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ጋር በመሆን በማይጠብሪ ግንባር ውቅን ተራራ ሥር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር የ2014 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን አክብረዋል።

በስፍራውም ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላና የምእራብ ዕዝ አዛዥ ሜጄር ጀኔራል መሰለ መሰረትን ጨምሮ የዕዙ አመራር አባላት አሸባሪው ህወሃት በከሃዲው ጀኔራል ምግበይ እየተመራ በውቅን ተራራ ላይ ያደረገውን ውጊያና የገጠመውን ኪሳራ በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በዚህን ወቅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሃት “አርሚ አንድ” በሚል ስያሜ በሰጠውና ራሱ ያዘጋጃቸው ዘጠኝ “ክፍለ ጦሮች”ና አንድ “ሻለቃ ኮማንዶ” ዋነኛ ዓለማ የኢትዮ-ሱዳንን ኮሪደር ማስከፈት መሆኑን ነው የገለጹት።

ኮሪደሩን ለማስከፈት ደግሞ ቀጥታ በሁመራ ከመሄድ ይልቅ በማይጠብሪ በኩል ቆረጣ በመፈጸም ጎንደርን ከተቆጣጠረ በኋላ መስመሩን ለማስከፈት ውጥን ይዞ መንቀሳቀሱን አንስተዋል።

“አርሚ አንድ” የተሰኘው ሃይል ይህን ሲያደርግ፤ “አርሚ ሁለት” የተሰኘው የአሸባሪው ታጣቂዎች ደግሞ በጋሸና እና በነፋስ መውጫ በፍጥነት በመንቀሳቀስ በደብረ ታቦር አድርጎ ጎንደርን ከባህር ዳር የመቁረጥ ውጥን ይዞ መንቀሳቀሱን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀኔራል ብርሃኑ አብራርተዋል።

ነገር ግን የመከላከያ ሠራዊቱ ይህን ቀድሞ በመገንዘብ ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በማይጠብሪ የተሰለፈውን “አርሚ አንድ” የተሰኘውን ሃይል “ከውቅን ተራራ ስር ቀብሮ ከጥቅም ውጪ አድርጎ ደምስሶታል” ነው ያሉት። 

ሠራዊቱ አብረውት ከተሰለፉ የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆንና የህዝብን ደጀንነት በመያዝ በጋሸና በኩል አድርጎ ባህርዳርን ከጎንደር ለመቁረጥ የመጣውን “አርሚ ሁለት” የተሰኘውን ሃይልም በአኩሪ ግስጋሴ ድባቅ እየመታው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። 

የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት በበኩላቸው “አርሚ አንድ” የተሰኘው የአሸባሪው ታጣቂ የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት ከንቱ ጥረት አድርጓል። ለዚህ እቅዱም ቀደም ብሎ በስደተኛ ስም ወደ ሱዳን ያሻገራቸው የአሸባሪ ቡድኑ ሃይሎችና የእርሱ ተላላኪ የሆኑ የቅማንት አክራሪ ታጣቂዎች ጋር በመሆን መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

“አርሚ አንድ” ጋር በቅንጅት ሲሰሩ የነበሩት ተላላኪ ቡድኖች “አርሚ አንድ“ በሚፈለገው ፍጥነት ሊመጣላቸው ባለመቻሉ ተስፋ በመቁረጥ በአማራ ክልል ምዕራብ አቅጣጫ ‘’ሽፋ’’ በተባለ አካባቢ ያልተሳካ ሙከራዎችን ማድረጋቸውንም ነው ጨምረው የገለጹት።

የአሸባሪ ቡድኑ የኢትዮ-ሱዳን ኮሪደርን ለማስከፈት የሚያደርገው ከንቱ ሙከራ ዋነኛ ዓላማ ለጥፋት ተልእኮ የሚሆኑትን የጦር መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማስገባት መሆኑንም ነው ያወሱት።

ነገር ግን ጠላት በማይጠብሪ ግንባር በ”ዘጠኝ ክፍለጦሮች” አዋቅሮ ያዘጋጀው ሃይሉ እንዳሰበው ሳይሆን ድባቅ ተመቶ መመለሱንም ሜጄር ጀኔራል መሰለ መሰረት ተናግረዋል።

በአውደ ውጊያው ካለቁ የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ሃይሎች በተጨማሪ በሽንፈት ሲሸሹ የነበሩ የሽብር ቡድኑ ሃይሎችና ቁስለኞች ይዘው እንዳይወጡ ተደርጎ ተከታታይ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህም በአስር ሺህዎቹ የሚቆጠሩ የጠላት ሃይል ተደምስሶ፤ የሽብር ቡድኑ የሀፍረት ካባ ተከናንቦ መመለሱን አብራርተዋል።

ሌሎች የምዕራብ ዕዝ አመራር አባላት፤ አካባቢው ካለው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፤ ከነበረው አየር ጠባይ አኳያ ውጊያው አልህ አስጨራሽ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጠላት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዋነኛው መስመር አድርጎ የያዘው የዓውደ ውጊያ ግንባር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እጅግ በርካታ ሃይሎቹን ያሰለፈ መሆኑን ነው ያነሱት።

“ውጊያውን ለማሸነፍ ወኔ፣ እልህና ቁርጠኝነት ያስፈለግ ነበር፤ ይህን ደግሞ ሠራዊቱ በሚገባ ተግብሮታል” ሲሉም ነው የተናገሩት። 

ሠራዊቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከህዝብ ማግኘቱን ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ በአውደ ውጊያው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያኮራ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

የአሸባሪው ህወሃት መንገድ ቆርጦ የኢትዮ-ሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት ያሰበው ቅዥትም ከንቱ ሆኖ መቅረቱን ነው የተናገሩት።

የምዕራብ ዕዝ አመራር አባላት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ እያደረገው ላላው ድጋፍ፣ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ እንደሆነው ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

አሸባሪው ህወሃት “አርሚ አንድ” በሶስት ኮሮች የተዋቀረ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ኮሮች ደግሞ በሶስት ክፍለ ጦሮች የተዋቀሩ መሆናቸውን በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌቴናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

እያንዳንዳቸው ክፍለጦሮች ደግሞ ከ1500 እስከ 2000 የሰው ሃይል እንዳላቸው ሌቴናል ጀኔራል ባጫ ገልጸዋል።