የኢትዮጵያ ወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ የቮሊቦል ውድድር ከቡርኪናፋሶ አቻው ጋር ይጫወታል

79

አዲስ አበባ  መስከረም 4/2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ከቡርኪናፋሶ አቻው ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል።

16 የአፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት 23ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ውድድር በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (ሲኤቪቢ) አዘጋጅነት በሩዋንዳ ኪጋሊ ከጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ በምድብ ሁለት ከቱኒዚያ፣ ደቡብ ሱዳንና ናይጄሪያ ጋር ነበር የተደለደለው።

ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎቹ ደቡብ ሱዳንን 3 ለ 2 ያሸነፈ ሲሆን፤ በቱኒዚያ 3 ለ 0 እና በናይጄሪያ 3 ለ 1 ተሸንፎ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም።

ከምድቡ ያላለፈው ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ከ9 እስከ 16 ያለውን ደረጃ ለመያዝ ከትናንት በስቲያ ከኒጀር አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 1 ተሸንፏል።

በኒጀር በደረሰበት ሽንፈት ምክንያት ቡድኑ ከ9 እስከ 16 ያለውን ደረጃ ለማግኘት ከሚደረጉ ጨዋታዎች  ወደ ከ13 እስከ 16 ያለውን ደረጃ ለማግኘት ወደ ሚደረጉ ጨዋታዎች ዝቅ ብሏል።

በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከቡርኪናፋሶ አቻው ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

የቡርኪናፋሶ ወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ዩጋንዳን 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፤ በአዘጋጇ አገር ሩዋንዳና ኬንያ በተመሳሳይ  3 ለ 0 እንዲሁም በብሩንዲ አቻው 3 ለ 1 ተረቷል።

የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በድጋሚ ከደቡብ ሱዳን ጋር 13ኛ እና 14ኛ ደረጃን ለማግኘት ነገ ጨዋታውን ያደርጋል።

ደቡብ ሱዳን ዛሬ ከታንዛንያ አቻው ጋር ጨዋታ ማድረግ የነበረባት ቢሆንም ተጋጣሚው ብሔራዊ ቡድን ለውድድር  ተሳትፎና ለሆቴል ማረፊያ ክፍያ ባለፈጸሙ ምክንያት በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን (ሲኤቪቢ) ከውድድሩ ውጪ እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት የ3 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግታለች።

የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ጨዋታ ሽንፈት ካጋጠመው የታንዛንያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከውድድሩ ውጪ በመሆኑ ምክንያት ቀጣይ ጨዋታ ሳያደርግ በፎርፌ አሸንፎ 15ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቅቃል ማለት ነው።

በ23ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ውድድር ዛሬ ሞሮኮ ከካሜሮን እንዲሁም ግብጽ ከቱኒዚያ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች ነገ የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ይፋለማሉ።

በተያያዘ ዜና 20ኛው የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ውድድር ትናንት በሩዋንዳ ጋሊ የተጀመረ ሲሆን ዘጠኝ አገራት በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።

በዚሁ መሰረት በምድብ አንድ አዘጋጅ አገር ሩዋንዳ ከሴኔጋል፣ ሞሮኮና ናይጄሪያ ጋር የተደለደለች ሲሆን ካሜሮን፣ ኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ቱነዚያና ዴሞክራቲክ ኮንጎ በምድብ ሁለት የሚገኙ አገራት ናቸው።

በምድብ አንድ ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች አዘጋጅ አገር ሩዋንዳ ሞሮኮን 3 ለ 1 ስታሸነፍ ናይጄሪያ ሴኔጋልን 3 ለ 0 ረታለች።

በምድብ ሁለት በተመሳሳይ ትናንት ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ብሩንዲን እንዲሁም ካሜሮን ኬንያን በተመሳሳይ 3 ለ 0 አሸንፈዋል።

የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ውድድር እስከ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ይቆያል።

በሩዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ቮሊቦል ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ አገራት እ.አ.አ በ2022 በሩሲያ በሚካሄደው የዓለም የቮሊቦል ውድድር አፍሪካን ወክለው ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ውድድር ሲሳተፍ የዘንድሮው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ የሴቶች ቮሊቦል ውድድር ሁለት ጊዜ ተሳትፏል።

እ.አ.አ በ1991 በግብጽ በተካሄደው አምስተኛው አፍሪካ የሴቶች ቮሊቦል ውድድር ስምንተኛ እንዲሁም እንደ በ1993 በናይጄሪያ በተካሄደው ስድስተኛው ውድድር ላይ ተሳትፎ አምስተኛ መውጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቱኒዚያ የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ውድድርን 10 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ፤ ግብጽ ስምንት ጊዜ ካሜሮንና አልጄሪያ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ውድድሩን አሸንፈዋል።

በሴቶች ኬንያ ዘጠኝ ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን የያዘች ሲሆን ግብጽና ቱኒዚያ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ የውድድሩን ዋንጫ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም