በአሸባሪው ሸኔ ለተፈናቀሉና ለአቅመ ደካሞች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ ተበረከተ

70

ነገሌ፣ መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) በምእራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት በሽብርተኛው ሸኔ ለተፈናቀሉና ለአቅመ ደካማ ወገኖች የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ አደረገ ፡፡

የገላና ወረዳ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ኢያሱ ጂኦ ለኢዜአ እንደገለጹት  ሽብርተኛው ሸኔ"የመንግስት ደጋፊ ናችሁ" በሚል ነዋሪዎችን በመፈረጅና ብሄር ከብሄር በማጋጨት በርካታ ሰዎችን ለመፈናቀል እየዳረገ ነው። 

ጽህፈት ቤቱ የወረዳውን ህዝብ በማስተባበር በጥፋት ቡድኑ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ በቡድኑ ለተፈናቀሉ ለ600 የአርሶና አርብቶ አደር ቤተሰብ አባላት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል ።

ለአርሶና አርብቶ አደሮቹ 40 የወተት ጊደሮች፣ ሁለት ቦንዳ የቀንና የሌሊት አልባሳት፣ 72 ኩንታል ስኳር፣ 4 ሺህ 200 ሊትር ዘይትና የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስና የንጹሃንን ሰቆቃ ለማስቆም የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግስት የጸጥታ ሃይል ተሰማርተው ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ሽብርተኛው ሸኔ በጉጂና ጌዴኦ ህዝቦች መካከል በቀሰቀስው የብሄር ግጭት ባለቤቴ ሞቶ የልጆች አሳዳጊ ሆኛለሁ፤ አሁን ላይ በቡድኑ ስለተዘረፍኩ ከብትም የለኝም" ሲሉ የደረሰባቸውን ጉዳት ገልጸዋል ።

"ሀገር የሚገነባው እርስ በእርስ በመረዳዳት እንጂ በመጠፋፋት አለመሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ የሰላም አማራጭን ሊከተል ይገባል" ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አቶ ገመዴ ገላ ናቸው።

አቶ ገመዴ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው "እርስ በእርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ አኩሪ ባህላችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም