በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

63

አሶሳ፤ መስከረም 03/ 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ፡፡

ድጋፉን ያመቻቹት  የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት እና ሌሎች ተቋማት በመተባበር መሆኑን የጽህፈት ቤቱ  ሃላፊ ወይዘሮ ከልቱም ባበክር ገልጸዋል።

የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተመቻቸውን ድጋፉ  በአሶሳ ከተማ እንዲሁም በአሶሳ ወረዳ አፋሲዝም እና አብረሃሞ ገጠር ቀበሌዎች ለሚኖሩ ወደ  600 ለሚጠጉ እናቶች እና ህጻናት በበዓሉ ዕለትና ትናንት ተከፋፍሏል፡፡

ድጋፉ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ ዱቄት፣ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ሲሆን  አጠቃላይ ግምታቸው ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙ የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት አመራሮች ህብረተሰቡ በአዲሱ ዓመት የመረዳዳት ባህሉን በተግባር በማሳየት አንድነቱን እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ድጋፉን ካገኙት መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም