በጅማ ከተማ ለ1ሺህ 439 ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ

58

ጅማ፣ ጷጉሜን 05/2013 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ 1ሺህ 439 ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ እህልና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ከድጋፉ ውስጥ ፈያ ኢንተግሬትድ ደቨሎፕመንት አሶሴሽን የተባለው ድርጅት  ለ139 አቅመ ደካማ ነዋሪዎች  87 ኩንታል ጤፍ፣ ሩዝና ማሽላ እንዲሁም  ለ500 ተማሪዎች ደግሞ የመማሪያ ቁሳቁስ የለገሰው ይገኝበታል።

የድርጅቱ  መስራችና ዳይሬክተር አቶ አንበሶ ቶላ በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ወቅት እንዳሉት፤ ድርጅቱ ዛሬ ለህብረተሰቡ ያደረጋቸው ድጋፎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ናቸው።

በየስድስት ወሩ ችግረኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች  የምግብ እህል የሚደግፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮ-ቴሌኮም የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ጅማ ቅርንጫፍ የችግረኛ ቤተሰብ ለ800 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር ድጋፍ አድርጓል። 

ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች  ከዘጠኝ  ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ መሆናቸውን የቅርንጫፉ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ካሳ ገልጸዋል።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቲጃኒ ናስር ድርጅቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ  መሰል የመረዳዳት ባህላችን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም