ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

88

ጳጉሜ 5/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላቸወን ስምምነት አደረጉ።

ስምምነቱ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኤድዋርድ ማካያ በተገኙበት ተከናውኗል።  

የሚኒስቴሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አማካሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሰፊ ስራዎችን በጋራ መስራት ያስችላል ብለዋል።

ዘርፉ ለአገር እድገት ከሚያበረክተው ሚና አኳያም የባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል የተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።  

ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በተለይም በስራ ፈጠራ፣ በሃብት አመንጪነትና በማህበረሰብ አቀፍ ችግር ፈቺነት ምርምሮች የረዥም ጊዜ ልምድ ያላት አገር ናት።

ይህም ኢትዮጵያ በቀጣዩ 10 ዓመት ለያዘችው የልማት እቅድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ገልጸዋል።     

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኤድዋርድ ማካያ በበኩላቸው፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ለአገር ልማት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ስምምነቱ ሁለቱ አገራት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራት እንዲችሉ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም