ያለፈው አመት ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም ጽናታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት ነበር

120

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 5/2013 (ኢዜአ) "አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን በአዲስ መንፈስ ከፍ የሚሉበት ዓመት እንዲሆን ልባዊ ምኞቴ ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመልካም ምኞት መልክት አስተላለፉ። ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአንድነት ጸንተን መቆም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

2013 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም  "ጽናታቸውንና መንፈሰ-ጠንካራነታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት ነው" ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ምልክት ጥሎ ማለፉን አመልክተዋል።

ሠራዊቱ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የተቃጣበትን ጥቃት በጀግንነት መመከቱን ጠቁመው፤ ሕዝቡም ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን አጋርነቱንና አክብሮቱን ማሳየቱን ገልጸዋል።

ይሁንና አሸባሪው "ሕወሓት የደቀናቸው ፈተናዎች አሁንም አላለቁም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወገኖቻችን ከአሸባሪው ቡድን ቀንበር ነጻ መውጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ተፈናቃዮች ወደ የቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህን ስናደርግ ቁስሎቻችን እንደፈወሱ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ የውጪ ጠላቶች ሴራና ተንኮል ለማክሸፍ በጋራ መቆምና መታገል እንደሚገባቸው ነው ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ የገለጹት።

ኢትዮጵያ ያገጣሟትን ፈተናዎች በመጋፈጥ የአገራችውን ሉላዓዊነትና ክብር ለማስጠበቅ በጽናት ለቆሙ ዜጎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

"ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን በማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት ጸንተን መቆም አለብን" ብለዋል።

ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ባለፉት ሶስት ዓመታት የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ ተሃድሶዎችን በማፋጠን "የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ አመት ኢትዮጵያውያን በአዲስ መንፈስ ከፍ የሚሉበት፤ እንዲሁም "በወንድማማችነትና በአንድነት የሚቁበት ዘመን እንዲሆን ልባዊ ምኞቴ ነው" ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአዲስ አመት መልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚክ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል

ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ውድ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ 

አስቀድሜ፣ ይህንን የ2014 አዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ ሠላምታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቴን በራሴና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስም ሳስተላለፍ ከፍ ያለ ክብርና ታላቅ ደስታ ይሰማኛል። አዲስ አመት በኢትዮጵያውያን መንፈስ የለውጥ መገለጫ እንደመሆኑ ከፀሃይ ብርሀን እና ከምንወዳት ኢትዮጵያ በቀለማት ያሸበረቀ መልክዓ ምድር ጋር ይመጣል። ይህም አዲስ አመት በአዲስ መንፈስ ከፍ የምትሉበት፣ እንዲሁም በወንድማማችነትና በአንድነት የምትደምቁበት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።

ባለፈው አመት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ አሰራርና ሙሌት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የአገራችንን ሉአላዊነት ለማጠበቅ ያለንን አንድነትና ቁርጠኝነት በሚያንጸባርቅ መልኩ አከናውነናል፡፡ ግድቡን በምንገነባበት ወቅትም በገንዘብም ይሁን በቴክኒክ ድጋፍ ሁላችንም የበኩላችንን በተሻለ ደረጃ ከማበርከት ወደኃላ አላልንም።በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባደረጉት ርብርብ እጅግ ተደስታቸለሁ።በሚቀጥሉት ዓመታትም የበለጠ አስደናቂ ውጤቶችን እንድንመዘግብ ይህንን ታላቅ ሃገራዊ ፕሮጀክት መደገፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የህዳሴው ግድብ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የአሸናፊነት ነጥቦችን እንድናስመዘግብ የጎላ ሚና የተጫወቱትን ዲፕሎማቶቻችንና ከተለያዬ ዘርፍ የተውጣጡትን ባለሙያዎቻችንን ልናደንቃቸውና ልናመሰግናቸው ይገባል። እንዲሁም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” የሚለውን እሳቤ ይዘን ባደረግናቸው ተከታታይ ውይይቶችና ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚመራውን የድርድር ሂደት እውን ለማድረግ እና የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲሆን የተደረገውን ጥረት እናደንቃለን። ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ ሙሌት ኢኮኖሚዊ እድገታችንን ለማነቃቃትና በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ያነገብነውን የብልጽግና ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ አንድ ትልቅ ምዕራፍን የተሻገርንበት ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ያስመዘገብነውን ስኬት እያዬን ዋናውና የመጨረሻ ግባችንን መርሳት አይኖርብንም። ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቀን አስተውለን በተባበረ ክንድ የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን።

ውድ ኢትዮጵያውያን፣ 

ያለፈው አመት ኢትዮጵያውያን የውስጥና የውጪ ተግዳሮችን በመቋቋም ጽናታቸውንና መንፈሰ-ጠንካራነታቸውን ከፍ አድርገው ያሳዩበት አመት ነበር፡፡

ከዚህም በላይ ህዝባችንን ከዳር እስከ ዳር ያስደነገጠው የጥቅምት 24ቱ የኢትዮጵያ ጠሉ ከሃዲ ቡድን የምሽት ጥቃት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ምልክትን ጥሎ ያለፈ ክስተት መሆኑን ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን አይረሱትም፡፡ በዚህ ደርዝ ባጣ ድፍረቱና ጨካኝ ድርጊቱ በሰሜን እዝ የነበሩ በርካታ ጀግና ወታደሮቻችንን አጥተናቸዋል፡፡ ያንን አሰቃቂ ሞት ከወታደሮቻችን አንዳቸውም አይገባቸውም።

ይሁንና የሀገራችን ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ህወሃት የተቃጡብንን ተግዳሮቶች በሚገባ በመመከትና ከጠላቶቻቸን በተቃርኖ የቆመ የተባበረ ህዝባዊ ግንባርን በመፍጠር ጀግኖቻችን ለከፈሉት መስዋትነት አክብሮትን አሳይተናቸዋል።

አሁንም ቢሆን በወያኔ የተደቀኑብን ፈተናዎች ገና አላለቁም፡፡ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያሉ ወገኖቻችን ከአሸባሪው ቡድን ቀንበር ነጻ መውጣታቸውንና ተፈናቃዮች ወደ የቀድሞ የመኖሪያ ስፍራቸው እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ይህን ስናደርግ በእርግጠኝነት ቁስሎቻችን ይፈወሳሉ።

በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ አረጋውያንን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ግፍ እና ኢሰብአዊ ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽኩ እነዚህን ትርጉም የለሽ ግድያዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሁሉም ሰላም ወዳድ የሆነ ሁሉ እንዲያወግዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ጠላቶቻችን እኛን ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነት ከመዳረጋቸው ባሻገር በኢኮኖሚያችንን ላይም መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍተውብናል። ሆኖም ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት እንዲያደናቅፉት በፍጹም መፍቀድ የለብንም፡።እነርሱ መሠረታዊ የፍጆታና ልዩ ልዩ የመገበያያ እቃዎችን በማከማቸት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬን ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች በማስተላለፍ የልፋታችንን ፍሬ ሊያሳጡን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ደባ ይበቃል የምንልበት ጊዜው አሁን ነው። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ዘመዶች ገንዘብ በምትልኩበት ጊዜ በሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋማት በመጠቀም ኢትዮጵያን እንድትደግፉ አሳስባለሁ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እውነትን ሰንቃችሁ ለአገራችሁ ኢትዮጵያ በታማኝነት እና ሉዓላዊነትዋ እንዲከበር በጽናት ከጎናችን ለቆማችሁ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላትና መላው የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥልቅ ምስጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።

ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፣ 

በመካከለኛው ምስራቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወገኖች እየደረሰባቸው ያለውን ችግር እንረዳለን። ለዚህም አስፈላጊውን እገዛ ከማድረግ ባለፈ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትንም ወደ ሀገራቸው መመለሳችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ የኮቪድ ወረርሽ ከስደተኞቹ ብዛት ጋር ተዳምሮ እርዳታ ለሚፈለጉ ዜጎቻችን ሁሉ ለመድረስ አቅማችንን ቢፈታተነውም በቻልነው ሁሉ ልክ እየተንቀሳቀስን ነዉ። በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከሀገር ውስጥና ከአለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሰራ ቃል እገባለሁ።

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

 
በርካቶች ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አቅማችንን ተጠራጥረውት የነበር ቢሆንም ለሰላም ጥልቅ ፍቅር ላለው ኢትዮጵያዊ ምስጋና ይግባና፣ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ከልካይነት፣ በነጻነት ድምጻቸውን የሰጡበትና አሻራ ያስቀመጡበት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ የምርጫው ውጤትም በአዲሱ አመት ወርሃ መስከረም መጨረሻ ልናቋቁመው ላለው አዲስ መንግስት የኢትዮጵያውያን የማስተማመኛና የማስረገጫ ማህተሞች ናቸው።

ይህንንም እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ብልጽግናንና ህብረትን መርጠዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት በማድረግ እና ባለፉት ሶስት አመታት የጀመርናቸውን ዘርፈ ብዙ ተሃድሶዎችን በማፋጠን የብልጽግና ህልማችንን እውን እናደርገዋለን።

በዚህ ወቅት ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን የማስተላልፈዉ ዋንኛ መልክት ራሷን የቻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን በማድረግ እጅ ለአጅ እንድንያያዝና በአንድነት ጸንተን እንድንቆም ነዉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራችን ዋና ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የተሃድሶ ሂደት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ለአገራችን የበለጸገ የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚመጥን ጠንካራና ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሰራተኞችን ይፈጥራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር አገራቸውን እንደ አምባሳደር እንዲቆሙ ጥሪ አቀርባለሁ። ተሃድሶው በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ዘርፎች የምንወዳትን አገራችንን ጥቅሞች ለመጠበቅ እና ለማስተዋወቅ ይረዳናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም አዲሱ አመት ለሁላችሁም የሠላም፣ የጤና፣ የደስታና የብልጽግና ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ፡፡ 

መልካም ዘመን፣

አመሰግናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም