በአፍሪካና ጃፓን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የበኩሌን ድጋፍ አደርጋለሁ ... አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ

91

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜ 5/2013(ኢዜአ)በአፍሪካና በጃፓን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ገለጹ።

አንጋፋዋ ዲፕሎማት የ2020 የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእውቅና ሽልማት ዛሬ ተበርክቶላቸዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ሽልማቱን አዲስ አበባ በሚገኘው የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በተካሄደው መርኃ ግብር በአፍሪካ ሕብረት የጃፓን ልዑክ አምባሳደር ሆሪዩቺ ቶሺሂኮ ተቀብለዋል።

ሽልማቱ አምባሳደር ቆንጂት በጃፓንና በአፍሪካ መካከል የጋራ መግባባት እንዲኖር ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል።

የአፍሪካና የጃፓን ግንኙነት እንዲጎለብት ባደረጉት አስተዋጽኦ ደስታ እንደሚሰማቸው አምባሳደር ቆንጂት ገልጸዋል።

የጃፓን አፍሪካ ልማት ፎርም(ቲካድ) በአፍሪካና በጃፓን መካከል ላለው የረጅም ጊዜ ትብብር እንደ ድልድይ ያገለገለ ነው ብለዋል።

ይህ ትብብር ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየጎለበተ መምጣቱንም አመልክተዋል።

ጃፓን ለአፍሪካ ልማት እያደረጋች ያለው ድጋፍ የሚደንቅ መሆኑንም ነው አምባሳደሯ የገለጹት።

አምባሳደሯ አሁንም የአፍሪካና ጃፓን በተለይም የአትዮጵያና ጃፓን ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር በሚቻለው ሁሉ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የጃፓን መንግስት ለሰጣቸው ክብርና እውቅናም ምስጋና አቅርበዋል።

በአፍሪካ ሕብረት የጃፓን ልዑክ አምባሳደር ሆሪዩቺ ቶሺሂኮ በበኩላቸው እ.አ.አ በ2013 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በነበረችበት ወቅት አምባሳደር ቆንጂት የጃፓን አፍሪካ ልማት ፎርም(ቲካድ) ስኬታማ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

እ.አ.አ በ2022 በቱኒዚያ የሚካሄደው ስምንተኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ፎረም(ቲካድ) በአፍሪካና በጃፓን እንዲሁም በኢትዮጵና በጃፓን መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረውም ገልጸዋል።

ፎረሙ የአፍሪካና የጃፓንን ትብብር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የጃፓን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሽልማት ከአምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት የአፍሪካ አቅም ግንባታ ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዮኮዜኪ ዩሚኮ ተበርክቷል።

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ለዶክተር ዮኮዜኮ የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።

ዳይሬክተሯ ሽልማቱን ያገኙት በጃፓንና በሌሎች አገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲዳብር ላደረጉት አስተዋጽኦ ነው።

አምባሳደር ቆንጂት ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግለዋል።

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አምባሳደሯ በዲፕሎማሲው መስክ ለነበራቸው አበርክቶ የእውቅና ሽልማት እንዳበረከቱላቸው ይታወቃል።

የአፍሪካ ኅብረት እውቅና የሰጣቸው ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል። 

የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ሆርዶፋ በቀለ የኢትዮጵያና ጃፓን ሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ2019 የጃፓን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ንዋይ ገብረ አብና ዶክተር አርከበ እቁባይ የክብር ኒሻን ሽልማት እንደተበረከተላቸው አይዘነጋም።


አዲስ አበባ በሚገኘው የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣የመንግሥትና የአፍሪካ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም