ሴት አመራሮች አገር ችግር በገጠማት ጊዜ የጥንት እናቶችን ብልሃትና ጀግንነት ሊደግሙት ይገባል

289

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜ 5/2013(ኢዜአ ) ሴት የአመራር አባላት አገር ችግር በገጠማት ጊዜ የጥንት እናቶች የተጠቀሙበትን ብልሃትና ጀግንነት በመድገም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።

ይህን የገለጹት የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማደረግ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊ ሴቶች ናቸው።

ሴት የሥራ ኃላፊዎቹ አገር ችግር በገጠማት ወቅት በአመራር ላይ ያሉ ሴቶች ኃላፊነታቸውን በብልሃትና በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶች አገር ችግር ሲገጥማት ብልሃትና ጀግንነታቸውን ተጠቅመው መሻገራቸውን ታሪክም ያስረዳናል ሲሉ ተናግረዋል።

አገር በችግር እየተፈተነች በመሆኑም በየዘርፉ ያሉ ሴት አመራሮች እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊትና የፀጥታ ሃይሎች የሚገባቸውን ክብርና እገዛ ከማድረግ ባሻገር ከቀያቸው የተፈናቀሉትን በማቋቋምና ወደ ሠላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ በማድረጉ ስራ ኃላፊነታችን ትልቅ ነው ብለዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው አገር በማዳኑ ተግባር ሴቶች ምንጊዜም የመጀመሪያ ተሰላፊዎች መሆናቸውን አውስተዋል።

በሕልውና ዘመቻው ሴት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሕይወታቸውን በመስጠት አንጸባራቂ ድል እያስመዘገቡ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

“በተለያየ የመንግስት ሃላፊነት ላይ የምንገኝ ሴቶችም ይህንኑ ማስቀጠል አለብን” ብለዋል።

በከፍተኛ የአመራርነት ኃላፊነት ላይ ያለን ሴቶች ለሌሎች “ዓርአያ ልንሆን ይገባናል” ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ናቸው።

የሴቶችን ችሎታ የመጠራጠር ሁኔታ አሁንም ይስተዋላል ያሉት ወይዘሮ መዓዛ ይሁንና የተሰጣቸው ከፍተኛ ኃላፊነት የመንግሥትን ጠንካራነት ያሳያል ብለዋል።

ይህ ተግባር ሊበረታታ የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል።

የሥራ ኃላፊዎቹ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።