አገራችን በ2013 ዓ.ም ያጋጠሟትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች በበሳል አመራር እና በዜጎቿ አንድነት መሻገር ችላለች

76

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜ 5/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ያጋጠሟትን የውስጥና የውጭ በርካታ ፈተናዎች በበሳል አመራር እና በዜጎቿ አንድነት መሻገር ችላለች ሲል የኢፌደሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለ2014 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት ምልዕክት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ያጋጠሟትን የውስጥና የውጭ በርካታ ፈተናዎች በበሳል አመራር እና በዜጎቿ አንድነት መሻገር ችላለች ያለው ምክር ቤቱ፤ በተለይ በ2013 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ መቻሉ፤ በውጭ አገራት ጣልቃግብነት ጭምር በአገራችን አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣብንን አደጋ ተቋቁመን ወደ 2014 ዓመተ ምህረት ተሻግረናል ነው ያለው።

“ይህም የሆነውም ሁሌም ኩራታችን በሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የክልል መንግስታት ልዩ ሀይሎች ፣ ሚሊሻ እና መላው ሕዝባችን እና አገር ወዳድ የዲያስፖራ ወገኖቻችን ባደረጉት ቆራጥ፣ ሁለንተናዊ ተጋድሎና ተሳትፎ ነው” በማለትም ነው ምክር ቤቱ በመልዕክቱ የገለጸው።

መላው ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቆ በጠነከረ አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት አንድነቱና አገራዊ ሉዓላዊነቱን ለማስከብር ያሳየው ተሳትፎ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ጥሪ አስተላልፏል።

አዲሱ 2014 ዓመት የሰላም፣ የጤና እና የብልፅግና ዘመን እንዲሆን የተመኘው ምክር ቤቱ፤”ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ሆነን በመነሳት እጅ ለእጅ ተያይዘን ለኢትዮጵያችን አንድነትና ብልጽግና በጋራ እንቁም” ሲል መልካም ምኞቱን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም