በሀገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የንባብ ፊደልን ለይቶ የማወቅና የሂሳብ ስሌት እውቀት ዝቅተኛ ነው

196

አዳማ፣ ጳጉሜ 05/2013 (ኢዜአ/) በሀገሪቱ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የንባብ ክህሎት፣ ፊደልን ለይቶ የማወቅና የሂሳብ ስሌት እውቀት ዝቅተኛ መሆኑን የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ አስታወቀ።

ኤጄንሲው በአስር ክልሎችና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እርከን ላይ ያሉ ተማሪዎች የፊደል ልየታ፣ የንባብ ክህሎትና የሂሳብ ስሌት ደረጃን ለማወቅ ጥናት ማካሄዱን ገልጿል።

የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ምዘና ጥናት አካሄዷል።

በጥናቱ በተለይ በ2ኛና 3ተኛ እንዲሁም ከ4ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የፊደል ልየታ፣ የንባብ እውቀትና ክህሎታቸውን ለማወቅ መካሄዱን ተናግረዋል።

"በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የማንበብ ክህሎትና ፊደልን ለይቶ የማወቅ እውቀት እጅጉን ዝቅተኛ ስለመሆኑ በጥናቱ አረጋግጠናል" ብለዋል።

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ ድምፅንና ፊደልን ለይቶ ከማወቅ አኳያ ሰፊ ችግር መኖሩን በጥናቱ መለየቱን የገለጹት ዶክተር ዲላሞ የጥናቱ ግኝት ውጤት ለመንግስትና ባለድርሻ አካላት መላኩን ገልጸዋል።

"ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ባለው የመጀመሪያ የትምህርት ዕርከን፣ ከ5ኛ እስክ 8ኛ ክፍልና በሁለተኛ ደረጃ ባሉት የትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የንባብ፣ የሂሳብ ስሌት ክህሎትና የትምህርት ጥራት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ተከታታይ ምዘና ይካሄዳል" ብለዋል።

ፖሊሲ አውጭዎችና ባለድርሻ አካላት በጥናቱ በተገኘ ውጤት ላይ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ላይ ክፍተት መኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

"በቀጣይ በትምህርት ስርዓቱ ወስጥ ያሉ ችግሮችን በየጊዜው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገምንና ፈጣን መፍትሄ እያስቀመጥን እንሄዳለን" ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የጥናት ግኝት ውጤቱን ያቀረቡት የትምህርት ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ኢፋ ጉርሙ እንዳሉት ጥናቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ተካሄዷል።

በጥናቱ ከ19ሺህ በላይ ተማሪዎች፣ ከ900 በላይ መምህራንና 484 ርዕሰ መምህራን መሳተፋቸውን የገለጹት ዶክተር ኢፋ በተለይ የ2ኛና የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች የንባብ ችሎታ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"የልጆቻችን የንባብ ችሎታ ከታችኛው የትምህርት እርከን ከመሰረቱ ካልተቃና ለሌላኛው የትምህርት ደረጃ መሰረት ሊሆን አይችልም" ብለዋል።

"በተለይ ፊደላትን በደቂቃዎች ማንበብና መለየት፣ አጭር ንባቦችን በተሰጣቸው ጊዜና በትክክል ማንበብ፣ የቃላት ንባብና ተዘውታሪ ቃላትን ከማወቅና ከመረዳት አንፃር ያሉበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

በጥናቱ ውጤት መሰረት ችግሩ በገጠርም ሆነ በከተማ በሴት ተማሪዎችም ሆነ በወንዶች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

"ማንበብ የማይችል ተማሪ ይዘን የትም መድረስ አንችልም፣ ተማሪዎች በቂ የመማሪያ መፅሐፍት የላቸውም፣ አንድ መፅሐፍ ለአምስት እየተጠቀሙ መሆኑን በጥናቱ ለይተናል፣ መንግስትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ሊፈልጉ ይገባል" ብለዋል።

በጥናት ውጤቱ ማንበብም ሆነ መፃፍ የማይችሉ ተማሪዎች በስፋት የተገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በመምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የንባብና ማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ተከታታይ ስልጠናና አቅም ግንባታ እንዲሁም ምዘና ላይ መንግስትና ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም