ስምምነት ላይ ሳይደረስ በአቢዬ ግዛት የቆየው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በሌላ መተካት የለበትም - ደቡብ ሱዳን

84

ዿጉሜ 05 /2013 (ኢዜአ) ደቡብ ሱዳን በግዛቲቱ ቀጣይ ዕጣ-ፈንታ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ሳይደረስ በአቢዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በሌላ መተካት የለበትም ስትል ገለጸች፡፡

ደቡብ ሱዳን በአቢዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በሌላ ከመተካቱ በፊት ስምምነት ላይ ልንደርስባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ማለቷ ተሰምቷል።

በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል ውዝግብ ያለበትን የአቢዬ ግዛት ቀጣይ እጣ ፈንታን በተመለከተ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት መውጣት የለበትም ስትል አስታውቃለች፡፡

የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ቢሮ ሀላፊ ጂያን ፒየሬ ላክሮክሲ በአቢዬ ግዛት የሚገኘውየኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በሚወጣበት ጉዳይ ላይ ከሁለቱም ሀገራት ሀላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የአቢዬ ግዛት ክትትል ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሀላፊ ዴንግ አሎር ከውይይቱ በኋላ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ከመውጣቱ በፊት በግዛቲቱ ቀጣይ ዕጣ-ፈንታ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ሊደረስ ይገባል የሚል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ሃላፊው አክለውም በቀጣይ ስምምነት ከተደረሰ እና የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ ሀይል በሌላ የሚተካ ቢሆን እንኳ ሁለቱም ሀገራት ዕውቅና የሰጡት እና የተስማሙበት ሊሆን እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በግዛቲቱ ቀጣይ ዕጣ-ፈንታ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማድረግም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም የሱዳን ትሪቡን ዘገባ አመልክቷል።

የሱዳን መንግስት "ከኢትዮጵያ ጋር በህዳሴ ግድብ እና በአልፋሽካ የድንበር ይገባኛል ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ በመግባታችን በአቢዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በሌላ ይተካልኝ" የሚል ጥያቄን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማቅረቧ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም