ሕንድ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ቁርጠኛ አቋም አላት - አምባሳደር ሮበርት ሺትኪንቶንግ

65

አዲስ አበባ ዻጉሜን 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሕንድ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ቁርጠኛ አቋም እንዳላት በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሺትኪንቶንግ ገለጹ።

አምባሳደር ሮበርት ሺትኪንቶንግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሁለቱ አገራት የወዳጅነት ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የቆየና ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል።  

የአገራቱ ግንኙነት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጭምር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ጠንካራ አጋርነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ለአብነትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1936 ኢትዮጵያ በጣልያን ስትወረር ህንዶች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን አስታውሰዋል።

አሁንም ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ አጋርነት እንዳላት ጠቁመው፤ ሕንድ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አረጋግጠዋል።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በመከረበት ጊዜ ሕንድ ይህንን አቋም በገቢር አሳይታለች ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄው በሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ራሷ ኢትዮጵያ ማፈላለግ እንዳለባትም ሕንድ አጽንኦት መስጠቷን ተናግረዋል።   

በሠሜኑ የአገሪቱ ከፍል በሚካሄደው ጦርነት በርካታ ሰዎች ለሰብዓዊ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያና የሕንድ ግንኙነት ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፤ ይፋዊ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1948 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም