በመዲናዋ በተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም ትልልቅ ድሎች ተመዝግበዋል -አቶ ዣንጥራር ዓባይ

54

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኢዜአ) የተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም በመዲናዋ ትልልቅ ድሎችን የተመዘገቡበት ዓመት መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ ተናገሩ።

ጳጉሜን 5 የድል ብሥራት ነጸብራቅ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።        

በሥነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይን ጨምሮ የከተማዋ የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፣የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሃና የሺንጉስ ተገኝተዋል።    

በመርሃ ግብሩ የመዲናዋ ወጣቶች በአረጋውያን ቤቶች እድሳት፣በትራፊክ፣በደም ልገሳ፣በችግኝ ተከላና በሌሎች መስኮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና እና አውቅና ተሰጥቷቸዋል።    

አቶ ዣንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለዝግጅቱ ታዳሚዎች የእንኳን አደረሳችሁ ካርድ ስጦታ አበርክተዋል።  

አዲስ አበባ ነዋሪዎች ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ ምርጫ በስኬት ማካሄዳቸውን አስታውሰው፤ ለዚህ ድልም የወጣቶች አበርክቶ ጉልህ እንደነበር አንስተዋል።

በተለይም ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸው በተጠናቀቀው ዓመት ከተገኙ ድሎች መካከል ጠቅሰዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ያሳዩት ደጀንነትንም እንዲሁ።       

ለሠራዊቱ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር በእያንዳንዳቸው ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ለሠራዊቱ ድጋፍ መደረጉንም ለአብነት ጠቅሰዋል።   

በተጠናቀቀው ዓመት የመዲናዋ ነዋሪዎች ለታላቁ የህዳሴ ግድብ  ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውንም ነው አቶ ዣንጥራር የገለጹት።    

የተመዘገቡ ስኬቶች ሳያኩራሩን በ2014 ዓ ም አዲሱ ዓመት ሊከናወኑ የሚገባቸው የቤት ስራዎች መኖራቸውን መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት።  

በአዲሱ ዓመት የኑሮ ውድነት፣የመኖሪያ ቤት እጥረት፣የሥራ አጥነት ችግሮችና አገልግሎት አሰጣት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመው፤  ለስኬቱም የመዲናዋ ነዋሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።  

በበጎ ፈቃድ ሲሳተፉ የነበሩ ወጣቶች በበኩላቸው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናና እውቅና በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ወጣት አብርሃም ኃይሉ ዓመቱን ሙሉ በበጎ ፈቃደኝነት የትራፊክ አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ገልጿል።

"ሰውን እንደመርዳት የሚያስደስት ነገር የለም" ሲልም ነው አስተያቱን የሰጠው።  

ወጣት ማህደር ዓመቱን አረጋያንና አቅመ ደካማ ወገኖችን በመርዳት እንዳሳለፈች ገልጻ፤ በሰራሁት ስራ ከእናቶች ምርቃት አግኝቻለሁ፤ ይሄ ደግሞ ለእኔ ትልቅ ውስጣዊ እርካታ ፈጥሮልኛል ብላለች ።    

ከ2013 ዓ.ም አምስቱ ጳጉሜን ቀናት መካከል አራቱ ኢትዮጵያዊነት፣አገልጋይነት ፣መልካምነትና የጀግንነት ቀን በሚል ስያሜ የተከበሩ ሲሆን፤ አምስተኛውና የመጨረሻዋ የጳጉሜን ቀን የድል ብሥራት ነጸብራቅ ቀን በሚል ስያሜ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም