ህዝብን ጋሻ አድርጎ የሚጮሄው አሸባሪ ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
ህዝብን ጋሻ አድርጎ የሚጮሄው አሸባሪ ድርጅት
አሸባሪው ህወሃትና በውጭ የሚኖሩ ደጋፊዎቹ በትግራይ ክልል “የሰብዓዊ እርዳታ ባለመድረሱ ህዝቡ ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተጋልጧል” በማለት ተደጋጋሚ ክስ በማቅረብ የዓለም አቀፉን ትኩረት ለመሳብ ይሞክራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ህዝብን ለታጣቂው ቡድን ስንቅ እንዲያዘጋጁ እያደረገ ይገኛል። በአንድ በኩል ለከፍተኛ ረሃብ ተጋለጧል እያለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለጦርነት ስንቅ እያዘጋጀ የጀግንነት ቀረርቶ የሚያሰማው ለምንድን ነው?
ሰሞኑን አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲፈጥር ለማድረግ በማሰብ “ረሃብ ተከስቷል፤ ሰዎችም ሞተዋል” የሚሉ ዜናዎችን በተከፋይ የማህበራዊ ሚዲያ አቀንቃኞችና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ እየሞከሩ ይገኛሉ።
የክሱ መነሻና የመገናኛ ብዙሃኑ ርብርብ ዓለማ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ለማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው።
ለአሸባሪው ህወሃት የዚህ ዓይነቱ ተግባር ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጀምሮ የሚፈጽመው ያልተቀየረ ስልቱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
በ1977 ዓ.ም በትግራይ ረሀብ ገብቶ ህዘቡ ሲሰቃይ የእርዳታ እህል ከመሃል አገር እንዳያልፍ መንገድ በመዝጋት የክልሉን ነዋሪዎች ለከፋ ጉዳት የማጋለጡ ጉዳይ ከመሪር ትውስታነቱ ባሻገር ለራሱ ጥቅም ይሰራ እንደነበር ግልጽ ማስረጃ ነው።
በጊዜው በድርቅ ለተጎዱት ከውጭ የመጣላቸውን አልሚ ምግብ፣ ምግብና ጨርቃ ጨርቅ በመዝረፍ ሱዳን ላይ ሲሸጥ የታዘቡ ዛሬም ያንን እንደሚደግም አይጠራጠሩም።
አሁን ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ በመዝጋት የትግራይ ህዝብ እርዳታ እንዳያገኝ እያደረጉት ነው። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች የተገኘውን በመቀማት “ልጆችህን ለዘመቻ ካላሰለፍክ የእርዳታ እህል አታገኝም” በሚል ሰበብና በዘረፋ ለታጣቂ ቡድኑ እንደሚሰጥ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ መልኩ በአፋርና አማራ ክልሎች ያካሄደውን ወረራ ለመፈጸም እየተጠቀሙበት መሆኑ ተስተውላል።
በአንድ በኩል “ሰብዓዊ እርዳታ የለም ህዝብ እያለቀነው” እያለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእህል መጋዘን ያቃጥላል፣ የተከማቸ እህልም ይዘርፋል። ለአብነት በቅርቡ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት የሚገኘው ለህጻናትና እናቶች የሚሆን የምግብ ክምችት ያለበትን የዩኒሴፍ የእርዳታ መጋዘን መዝረፉ መጥቀስ ይቻላል።
ንጹሀንን በጅምላ የመጨፍጨፍ፣ መንደሮችን የማውደም፣ ከብቶችን በመግደል፣ የእህል ማከማቻዎችን የማቃጠል፣ ተቋማትን የመዝረፍ ወንጀሎችን መገለጫ ባህሪው የሆነው አሸባሪው ሕወሃት፤ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን መጋዘን በመዝረፍና ዜጎች እንዲራቡ በማድረግ “ህዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው” የሚል አቤቱታ ማሰማት በግልጽ የሚስተዋል ጉዳይ ነው።
ቀደም ብሎ በአማራ ክልል የሚገኘውን የአሜሪካ ተራድኦ ደርጅት (ዩ.ኤስ.አይ.ዲ) መጋዘን መዝረፉን ድርጅቱ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የአሸባሪው ህወሓት አባላት ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚገኙትንና ለአስቸኳይ እርዳታ የሚውልን የእህል ክምችት መዝረፉቸውን በግልጽ ቢናገሩም የወሰዱት አቋም የለም። የተዘረፈው እርዳታ ግን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሚውል እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ደግሞ በአሸባሪው ህወሃት መጋዘን ውስጥ ታጣቂ ለመቀለብ የተቀመጠ የእህል ክምችት እንዳለ ያመለክታል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰበ ይሄ ይጠፋዋልን?
ይህ ብቻ ሳይሆን የአሸባሪ ህወሃት ልሳን በሆኑት መገናኛ ብዙሃን ለታጣቂው ቡድን ህዝቡ ስንቅ እያዘጋጀና የደጀንነት ተግባር እየፈጸመ መሆኑን እየገለጸ ነው። ታጣቂው በቂ ስንቅ እንዳለው የሚናገርና መጋዘኖችን ዘርፎ የሚያከማች አሸባሪ ድርጅት እንዴት ስለረሃብ ሊያነሳ ይችላል?
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ አሸባሪው ህወሃት "በትግራይ ክልል ረሃብ እንደተከሰተ በመግለጽ እየከሰሰ ባለበት አንደበቱ ለአሸባሪ ታጣቂዎቹ ደግሞ ‘በቂ ስንቅ ተዘጋጅቷል’ በማለት እርስ በርሱ የሚጣረስ የሀሰት መረጃ እያሰራጨ ነው” በማለት የገለጹትን ያረጋግጣል።
የፌዴራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ካደረገ በኋላ ለትግራይ ክልል ከ18 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንዲደርሱ ማድረጉን መረጃዎች ያረጋግጣሉ።
በዚሁ መሰረት ትግራይ ክልል ከ14 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ እህል እና ከአራት ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው እንዲደርሱ ተደርጓል።
እነዚህ የሰብዓዊ እርዳታዎች ለህዝብ እንዲደርስ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል። ነገር ግን የተላከው እርዳታ ለተገቢው ሰው ስለመድረሱ ሳያረጋግጡ “የእርዳታ እህል አልቋል፤ ህዝብ ሊያልቅ ነው” በሚል በተደጋጋሚ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሚናገሩት ከእውነታው በላይ ምንድን ነው የሚያስጨንቃቸው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
እንደውም የአሸባሪ ቡድኑ አፈቀላጤዎች “መንግስት የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ በመከልከሉ ምክንያት በክልሉ ረሃብ እየተከሰተ ነው” በማለት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አደናግረው ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጥሩ በእውነታ ላይ ተመስርተው ከማጋለጥ ይልቅ መልሰው ማስተጋባቱን መምረጣቸው “ለምን?” ያስብላል።
እዚህ ላይ ግን አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ነዋሪዎች በደቦ አሰማርቶ ስንቅ እያዘጋጀ፣ እህል ሞልቷል እያለና ጦርነት እየጎሰመ ልሳናቱ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ሲያስተላልፉ የተመለከተ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋም ጥያቄ ያነሳ የለም። ለምን?
አሸባሪው ህወሃት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም የሽብር ቡድኑ ከምስረታው ጀምሮ የሚጠቀመው 'ልዩ መገለጫ' መሆኑንም አጽንኦት ይሰጡታል የሰላም ምኒስትሯ።
ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከክልሉ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወራት የሚሆን የእሀል ክምችት ማስቀመጡን፣ ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች በአፋር በኩል እንዲገባ ማድረጉ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጡ “ህዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው” በሚል የአሸባሪው ህወሃት አስተሳሰብ በተደጋጋሚ እያራመዱ ይገኛሉ።
“የሕወሓት ቡድን በአሁኑ ወቅት ሁለት የሚጣረሱ ነገሮችን እየተናገረ ነው። በአንድ በኩል የትግራይ ክልል ሕዝብ በረሃብ እየተሰቃየ ነው ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በርካታ መጠን ያለው ስንቅ ለክልሉ ሚሊሻ ሲያዘጋጅ ይታያል። ይሕ ሁለቱ የሚጋጭ ድርጊት ነው” በማለት የሰላም ሚኒስትሯ የገለጹት ለዚሁ ነው።
አሸባሪው ህወሃት ከምስረታው ጀምሮ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ የመጠቀም ህዝብን ጋሻ አድርጎ የሚጮህ አሸባሪ ድርድት መሆኑን ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው።
የአሁኑን አጋጣሚ እንደመልካም እድል በመቁጠር "የፌዴራል መንግስት በክልሉ ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ሲል" መክሰሱ ብዙም አይደንቅም። ከዚህ ይልቅ ለየት የሚያደርገው ጉዳይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ትክክል አይደለም፤ ረሃብን እንደጦር መሳሪያ በመጠቀም ህዝብን እየጎዳህ ነው” በማለት እውነተኛውን ነገር ለመንገር አለመቻሉ ነው።
አሸባሪው ህወሃት "በህዝብ የሚነግድ ቡድን መሆኑ ይታወቃል፤ መንግስትን መክሰስ የሚያስችል ምንም ሞራል የለውም" ሊኖረውም አይችልም በማለት ነው የሰላም ሚንስትሯ እውነታውን የገለጹት።