ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታል የማውደም ድርጊት በጦር ወንጀልኝነት መታየት አለበት – አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴ

237

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሃት “ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት እጅግ አስነዋሪና በጦር ወንጀለኝነት መታየት ያለበት ድርጊት ነው” ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ።

“ማን ከማን ጋር እንኳ እንደተጋጩ የማያውቁ ህጻናትን ትምህርት ቤት ማውደም በምን ይገላጻል?” በማለት ነው በምሬት የጠየቀው።

ኢትዮጵያዊያን ፈተና በበዛባቸው ቁጥር እንደ አለት የሚጠነክሩ ህዝቦች መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበት ወቅት መሆኑን የተናገረው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ፤ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን ፃግብጂ ወረዳ በዳስ ጥላ ለሚማሩ ህጻናት ያስገነባው ትምህርት ቤት በመውደሙ እጅግ እንዳዘነ ገልጿል።

ትምህርት ቤቱ ከ500 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ህጻናት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል በፈጸሙት ወረራ ካወደሟቸው የህዝብ ሃብቶች መካከል ፃግብጂ ወረዳ ህጻናትን ከዳስና የድንጋይ መቀመጫዎች ያላቀቀው የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ትምህርት ቤት ይገኝበታል።

አትሌት ሻለቃ ሃይለ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ የዋግ ኽምራ አካባቢ ለረጅም ዘመናት ልማት ርቆት በእጅጉ የተረሳ ነበር።

የነገ ተስፋ ያላቸው ህጻናት በዚህ ዘመን ሊሆን ይችላል ተብሎ በማይታመን መልኩ በዳስ ጥላ ስር ሲማሩ መቆየታቸውን አስታውሶ፤ “ይህ ጉዳይም እጅግ ስላሳዘነኝ ትምህርት ቤቱን ገንብቼ ለአካባቢው ህዝብ አስረክቤያለሁ” ብሏል።

ትምህርት ቤቱን ለመገንባት ከገንዘብ ወጪ በላይ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የሚገልጸው አትሌቱ፤ “የትምህርት ቤቱ መውደም በአካባቢው ማህበረሰብ ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ይቆጠራል” ብሏል።

ከዚህ ቀደም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል በከፈተው በሃይሌ ሪዞርት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሶ እንደነበር አስታውሶ፤ በዳስ ለሚማሩ ህጻናት በተሰራው ትምህርት ቤት የደረሰው ውድመት ግን እጅግ እንዳሳዘነው ተናግሯል።

የትምህርት ቤቱ መገንባት በርካታ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እንዳደረገም ነው ያብራረው።

ነገር ግን ህጻናቱና ቤተሰቦቻቸው ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ ትምህርት ቤቱ መውደሙ እጅግ አሳዛኝ ክስተት መሆኑንም ተናግሯል።

“ማን ከማን ጋር እንኳ እንደተጋጨ የማያውቁ ህጻናትን ትምህርት ቤት ማውደም በምን ይገላጻል” ሲል የሚጠይቀው አትሌቱ፤ በድርጊቱ አትሌቱን ጨምሮ የድርጅቱ ሰራተኞች እጅግ ማዘናቸውን ነው የጠቆመው።

አትሌቱ ያስገነባውን ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች መውደማቸውን ጠቅሶ፤ ይህም የአሸባሪው ህወሃትን “የክፋት ጥግ ያሳያል” በማለት አስረድቷል።

በየትኛውም ዓለም በሚካሄዱ ጦርነቶች ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችን ዒላማ ማድረግ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑንም ተናግሯል።

“ማንም ኢትዮጵያን አፈርሳታለሁ ብሎ ስለጮኸ ኢትዮጵያን ማፍረስ አይችልም” ሲል ገልጾ፤ “ኢትዮጵያውያን ፈተናዎች በበዙ ቁጥር እንደዓለት እየጠነከሩ እንደሚሄዱ አሁን ያለንበት ወቅት የሚያሳየን ይህንኑ ሃቅ ነው” ብሏል።

ፋሺስት ጣልያንና የዚያድ ባሬ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሞከሩት “ኢትዮጵያ በውስጥ ተዳክማለች” በሚል አስበው እንደነበር አስታውሶ፤ ውጤቱ ግን በተቃራኒው መሆኑን አብራርቷል።

ኢትዮጵያ ስትነካ ኢትዮጵያዊያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዳር ዳር አንድ ሆነው ተነስተዋል፤ “ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል” በማለት የተናገረው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ፤ “ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚቻለው ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ማጥፋት ከተቻለ ነው” ብሏል።