ከህልውና ዘመቻው ድጋፍ ጐን ለጎን የመኸር ምርታችንን በእጥፍ ለማሳደግ እንሰራለን - የግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶ አደሮች

60

ፍቼ ጳጉሜን 3/2ዐ13 (ኢዜአ) የህልውና ዘመቻውን በሚያስፈልገው ሁሉ ከመደገፍ ጎን ለጎን የመኸር እርሻ ምርታችንን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራን ነው ይላሉ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ኢዜአ ያነጋገራቸው የግራር ጃርሶ ወረዳ አርሶ አደሮች።

በዞኑ በሰብል ከተሸፈነው መሬት ከአስር ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በወረዳው የወርጡ ቀበሌ አርሶ አደር አዱኛ ቶልቻ የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ባለፈ ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የህልውና ዘመቻውን እያገዙ ናቸው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም ከአንድ ሄክታር በብተና ከዘሩት የጤፍ ማሣ ከአስራ ስምንት ኩንታል ያልበለጠ ምርት እንደሚያገኙና በአሁኑ ወቅት ምርጥ ዘር በመጠቀምና በመስመር በመዝራታቸው በእጥፍ ለማምረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሌላው የዚሁ ቀበሌ የአካባቢ ሚሊሺያና አርሶ አደር ተስፋዬ ቦቼ ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን ሰጥተው የህልውና ዘመቻውን እየደገፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የእርሻ ማሳቸውን ከመንከባከብ በተጨማሪ የተሻሻሉ አሰራርን በመከተላቸውና የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው የሰብሉና የቡቃያው የእስከ አሁን ይዞታ በጣም ጥሩ በመሆኑ ከቀደመው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የቶርበን አሼ ቀበሌ አርሶ አደር ሰይፉ አደሬ በበኩላቸው በመስመር መዝራት አድካሚ እንደሆነ በማሰብ ለሁለት አመታት ተግባራዊ ሳያደርጉ መቆየታቸው ይናገራሉ።

የጐረቤቶቻቸውን ምርት በማየት ዘንድሮ በቁጥት በመነሳሳት ለመጀመሪያ ጊዜ አሰራሩን ተግባራዊ በማድረጋቸው የተሻለ ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸውም ተናግረዋል፡፡ 

የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ምክርና እገዛዎች ለእርሻ ስራቸውም እንደረዳቸው አመልክተዋል፡፡

አምና በብተናና በመስመር ዘርቼ ነበር ያሉት የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ገዝሙ በዳኔ በብተና ከዘሩት 13 ኩንታል ጤፍ በሄክታር ሲያገኙ በመስመር ከዘሩት ከ30ኩንታል በላይ በማግኘታቸው ዘንድሮ ሁሉንም ማሳቸውን በመስመር በመዝራት ከአምናው እጥፍ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተሻሻሉ አሰራሮች ማዳበሪያና ዘር እንዳይባክን ከማስቻል በተጨማሪ ለአረም የተጋለጠ ባለመሆኑ ጊዜና ጉልበታቸውን እንደቆጠበላቸው አመልክተዋል፡፡

እንደ ዞን የህልውና ዘመቻውን በልዩ ልዩ መንገድ ከመደገፍ በተጨማሪ በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለመጨመር በሰብል ከተሸፈነው 455ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ42ዐሺህ በላይ የተሻሻሉ አሰራሮችን የተከተለ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ ገልፀዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለፃ በመስመር የተዘራው በእቅድ ከተያዘው ከ97 በመቶ በላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በምርት ዘመኑ በሰብል ከተሸፈነው መሬት ከአስር ነጥብ አምስት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ የተለያዩ ድጋፎች ለአርሶ አደሩ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ 

በእርሻ ስራው 176ሺ 68ዐ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን በጥቂት ቀበሌዎች ከታየው የዝናብ እጥረት በስተቀር በአብዛኛው የዞኑ አካባቢዎች ለእርሻ ስራ ምቹ የሆነ ዝናብ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

አምና በዞኑ በሰብል ከተሸፈነው ከ7 ነጥብ 5ሚሊየን ኩንታል የሚበልጥ የሰብል ምርት የተገኘ ሲሆን በዘንድሮ አመት የዝናቡ መስተካከልና የተሻለ የግብአት አጠቃቀም በመኖሩ ምርት ይጨምራል የሚል የባለሙያዎች ግምገማ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም