የልዩ ፍላጎት ሞዴል ትምህርት ቤት ተመረቀ

123

ዲላ ፤ ጳጉሜ 3/2013 (ኢዜአ). በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተገነባ የልዩ ፍላጎትና መሰረታዊ የተቀናጀ የጎልማሶች ሞዴል ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ።

 ትምህርት ቤቱ የተገነባው "ፒፕል ኢን ኒድ " በተሰኝ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባደረገው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሆኑን በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል።

ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው ለተገለሉና ልዩ ፍላጎት ለሚሹ ከ250 በላይ ሴት ተማሪዎችና ወላጆቻቸውን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

የድርጅቱ የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አማረ ደምሴ በወቅቱ እንዳሉት፤  ድርጅቱ በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ውሰጥ ከ2 ሺህ በላይ ሴቶች መማር እንዲችሉ እየደገፈ ነው።

በወናጎ ወረዳ ሞኮኒሳ ቀበሌ ተገንብቶ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሞዴል ትምህርት ቤት  የዚሁ ድጋፍ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለመጪው የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት የተዘጋጀው ይኸው ትምህርት ቤት ስድስት የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፀሐፍትና የአስተዳደር ስራ መገልገያዎች አካቶ መደራጀቱ  አመልክተዋል።

የወናጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ ጌታሁን በበኩላቸው ፤ በአከባቢው  ልዩ ፍላጎት ላላቸው ታዳጊዎች የነበረውን የትምህርት ቤት ችግር በማቃለሉ ረገድ ሞዴል ትምህርት ቤቱ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደር ትምህርት ቤቱ የተገነበለትን ዓላማ ከግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመጥቀስ ለድርጅቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በምረቃ ሥነርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ተሻለ ደስታ ፤ በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና  በአካል ጉዳትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች  ምክንያቶች በክልሉ በርካታ ሴቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

ሞዴል ትምህርት ቤቱ ልጆችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ በተለይም ልዩ ፍላጎት የሚሹ ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት  እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

ቢሮው የትምህርት ቤቱን ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከማስፋት ባለፈ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት፤  ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስትና የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም