የንፋስ መውጫ ሆስፒታል በተያዘው ሳምንት መጨረሻ በከፊል አገልግሎት ይጀምራል

221

ባህር ዳር ጳጉሜን 3/2013 ( ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት የደረሰበት የንፋስ መውጫ ሆስፒታል በተያዘው ሳምንት መጨረሻ በከፊል አገልግሎት እንደሚጀምር የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አስታወቁ።

 ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ያደለው ጀምበር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  ሆስፒታሉ ለወላድ እናቶች፣ ለህጻናትና ለተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል።

አገልግሎቱን ለማስጀመር የሕክምና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች መመለሳቸውን ገልጸው፤  ለህክምና የሚያገለግሉ አልጋዎች፣ ፍራሾችና ብርድ ልብሶች ከአራት ዩኒቨርሲቲች በድጋፍ መገኘቱን አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉለት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

የሽብር ቡድኑ የሆስፒታሉን የመመርመሪያ፣ የቀዶ ህክምና፣ የላውንደሪ ማሽኖችንና መድኃኒቶችን የቻለውን ዘርፏል፣ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል ነው ያሉት።

ለመቄትና ስማዳ ወረዳዎች ጭምር የሚያገለግለው ሆስፒታል ወላድ እናቶችን ጨምሮ  ተመላላሽና ድንገተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችን ተቀብሎ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ዶክተር ያደለው አስታውሰዋል።

ሆስፒታል አሸባሪው ቡድን በፈፀመው ወረራና ባደረሰው ውድመት ተገልጋዮች ለችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የአከባቢው  ነዋሪ ወይዘሮ ሃብታም ወርቁ ፤  ”አሸባሪው ቡድን በፈፀመ ወረራና ውድመት አራተኛ ልጃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ህክምና ባለሙያ እርዳታ  በቤታቸው ለመውለድ ተገደድኩ’’ ነው ያሉት።

የአሁኑ ልጃቸውን በልምድ አዋላጅ በስቃይ መገላገላቸውን አሰታወሰው፤ መንግሥት ሆስፒታሉን ፈጥኖ አገልግሎት እንዲያስጀምረው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ክርክም እሸቴ ልጃቸው  በሆስፒታሉ የነርቭ ሕክምና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ አቅም በማጣታቸውና የሚወስደው መድኃኒት አቅርቦት በመቋረጡ በሕመም እየተሰቃየ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ሆስፒታሉን የተሟላ አገልግሎት በመስጠት መሰል ችግር ያለባቸውን ወገኖች እንዲታደግ አመልክተዋል።

የንፋስ መውጫ ሆስፒታል  በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ይገኛል።