በጋሞ ጎፋ ዞን ዘንድሮ የሚሰጠውን ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች በራስ መተማመን እንዲሰሩ ወላጆች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

71
አርባምንጭ ግንቦት 8/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን ዘንድሮ የሚሰጠውን ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና ተማሪዎች በራስ መተማመን መንፈስ እንዲሰሩ ወላጆችና አሳዳጊዎች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። ዞኑ በኩረጃ አስከፊነት ዙሪያ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት እየተሰጠ ነው። የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሔ ቦዳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ ከ147 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዘንድሮው ክልላዊና ብሔራዊ ፈተና ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ወላጆች ፣ አሳዳጊዎችና መምህራንም በኩረጃ አስከፊነት ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው ተማሪዎች ፈተናውን በራስ መተማመን መንፈስ እንዲሰሩ አስፈላጊውን ምክርና ትምህርት ሊሰጧቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ተማሪው በሰራው ልክ ውጤት እንዲያገኝ በዘንድሮ ብሔራዊ ፈተና "አንድ ተማሪ በአንድ ወንበር" የሚል መርህን ለመተግበር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በአርባምንጭ ከተማ የብሩህ ተስፋ ትምህርት ቤት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር ወርቁ ኪዳኔ በሰጡት አስተያየት ኩረጃ ለተማሪውም ሆነ ለአገር ልማት ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ተማሪዎች የዘንድሮውን ብሄራዊና ክልላዊ ፈተና በራስ የመተማመንና ከኩረጃ በፀዳ ሁኔታ እንዲፈተኑ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በአባያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ መምህራን ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አለሚቱ ሽፋው በበኩላቸው "ኩረጃ ከፍተኛ የሰነ ምግባር ጉድለት በመሆኑ ተማሪዎች ከዚሁ አኩይ ተግባር እንዲታቀቡ ትምህርት እየተሰጠ ነው" ብለዋል። ከትምህርቱ ባሻገር ድርጊቱን በሚፈጽሙ ተማሪዎች ላይ በህግ ጭምር እንዲጠየቁ መግባባታቸውን ገልጸዋል። የአርባምንጭ የርሆቦት ትምህርት ቤት ተማሪ ታማኝ መኮንን በሰጠው አስተያየት ኩረጃን የሚያበረታቱና የሚያውኩ ጉዳዮችን መንግስት ለይቶ ሊቆጣጠራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይ የተማሪዎችን በራስ መተማመን አቅም የሚሸረሽሩ አሉቧልታዎችም ከወዲሁ ሊገቱ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ በዞኑ ከሳምንት በፊት የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እስከ ብሄራዊ ፈተና መዳረሻ የሚቆይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም