ፌዴራል ፖሊስ በአገር ህልውና ዘመቻው አንጸባራቂ ድል እያስመዘገበ ይገኛል

235

ጳጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ በአገር ህልውና ዘመቻው በተሰለፈባቸው ግንባሮች ሁሉ አንጸባራቂ ድል እያስመዘገበ ነው።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ሰርጎ በመግባት በንፁሃን ላይ ጅምላ ግድያ በመፈፀም፣ ንብረት በመዝረፍና የህዝብ መገልገያ ተቋማትን በማውደም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ፈፅሟል።

የዚህን አገር አፍራሽ ሃይል እኩይ ተግባር ለመቀልበስ ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በተለያዩ ግንባሮች እየተፋለመ ይገኛል።

የፌዴራል ፖሊስ አባላት በተሰለፉባቸው ግንባሮች ሁሉ አንጸባራቂ ድል እያስመዘገቡ መሆኑን በወሎ ግንባር የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ አንድ ከፍተኛ መኮንን ገልጸዋል።

“አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶችን ፈጽሟል” ያሉት ሃላፊው፤ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን እያሳደዱት መሆኑን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በደቡብ ወሎ ወረባቦ አድርጎ ኮምቦልቻና ደሴን ተቆጣጥሮ ባቲ ለመግባት ያደረገውን ሙከራ በማክሸፍ ሂደት ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያና ከልዩ ሃይሎች ጋር በመሆን እቅዱን እንዳመከነበት ገልጸዋል።

በአገር ህልውና ዘመቻው የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ አሁንም ታላቅ ጀብዱ እየፈጸሙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፌዴራል ፖሊስ ታላላቅ የህዝብና የመንግስት ተቋማትን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ ሂደት የላቀ ጀብዱ ለመፈፀም ሁሌም ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።