የንግዱ ማህበረሰብ ሕግ ተከትሎ በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል -ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ

65

ሀዋሳ ጷጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) የሃዋሳ ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ አሳሰቡ ፡፡

ምክትል ከንቲባው ዛሬ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገር ለማፈራረስ አልመው ከከፈቱት ጦርነት ባለፈ በዋጋ ንረትና በተለያዩ መንገዶች ህዝቡን ለመጉዳት የኢኮኖሚ አሻጥሮችን እየፈጠሩ  ይገኛሉ።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ያለምክንያት ዋጋ በመጨመር በአቋራጭ ለመክበር የሚጥሩ አንዳንድ ነጋዴዎችም ከእነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያልተናነሰ ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን ተናግረዋል።

የሃዋሳ ከተማ ነጋዴዎች የእዚህ ተግባር ተባባሪ ሳይሆኑ በሕግና ሥርዓት ብቻ ሰርቶ በማትረፍ የሀገር አለኝታነቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ሳይቸገር እንዲያከብር የንግዱ ማህበረሰብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።  

የከተማዋ የንግድና አስተዳደር ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይሉ የቴራ በበኩላቸው፤  በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ በተደረገ ክትትል ያልተገባ ዋጋ ጨምረው በተገኙ 203 ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል

"ከዚህ ጎን ለጎን የንግድ ፈቃድ የሌላቸው 899 ነጋዴዎች ፈቃድ አውጥተው ወደ ሕጋዊ አሰራር እንዲገቡ ተደርጓል" ብለዋል።

አሁን ያለውን የዋጋ ንረት በመከላከል ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው ያሉት።

በተለይ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ምርት በብዛት እንዲያቀርቡ የገበያ ቦታን ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አየለ አዴላ በሰጡት አስተያየት፤  አሁን ባለው የዋጋ ንረት የተነሳ ህብረተሰቡ በእጅጉ እየተጎዳ መሆኑን ገልጸዋል ተናግረዋል::

"ይህን የሚያስተካክለው አስተዳደሩ ወይም የፀጥታ አካል ብቻ ሳይሆኑ እኛም የሚጠበቅብንን በመወጣት የህብረተሰቡን ችግር መጋራት ይኖርብናል" ብለዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሕይወት መቻል በበኩላቸው፤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከተማ አስተዳደሩና ነጋዴው ተናበው መስራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

የተረጋጋ ገበያ ኖሮ የህብረተሰቡ ችግር እንዲቃለል በሚጠበቅባቸው ሁሉ ከተማ አስተዳደሩን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ  የሃዋሳ ከተማ የንግዱ ማህበረሰብና ሴክተር ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም