የጎንደር ከተማ እስልምና ምክር ቤት አሸባሪው ህወሃት ያደረሰውን ውድመት አወገዘ

245

ጎንደር፣  ጳጉሜ 3/2013 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ እስልምና ምክር ቤት የህወሃት የሽብር ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በዜጎች ላይ ያደረሰውን ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት አወገዘ።

ምክር ቤቱ ለህልውና ዘመቻው የከተማውን ሙስሊም ማህብረሰብ በማስተባበር በግማሽ ሚሊዮን ብር ወጪ የደረቅ ስንቅ ዝግጅት ዛሬ አስጀምሯል።

የምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ሀጂ አደም አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ የወረራ አላማ ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ያነገበ መሆኑን በገሃድ ያሳየ ነው።

ወራሪው ሃይል በሃይማኖት ተቋማትና በእምነቱ መሪዎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ምክር ቤቱ አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጸዋል።

የሙስሊሙ ማህብረሰብ የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ ልጆቹን መርቆ ወደ ግንባር ከመላክ ጀምሮ በደጀንነት በመሳተፍ ለሰላም የሚከፈለውን ማናቸውንም አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በተጨማሪም 200 የሚደርሱ የምክር ቤቱ አባላትና የእምነቱ ተከታዮች ለሰራዊቱ ደም በመለገስ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በከተማው የሚገኙ በርካታ ሙስሊም ሴቶችን በማስተባባር በዛሬው እለት የደረቅ ስንቅ ዝግጅት እንዲጀመር ማድረጉንም አስታውቀዋል።

በደረቅ ስንቅ ዝግጅቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት ወይዘሮ ፋጢማ ጌታሁን በበኩላቸው እኛ ሙስሊም ሴቶች ለህልውና ዘመቻው በግንባር ለሚፋለሙ ወገኖቻችን ደረቅ ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታንን በተግባር እያረጋገጥን ነው ብለዋል።

የህወሃት የሽብር ቡድን በወገኖቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያና የሴቶች መደፈርን በማውገዝ ቁጭት አድሮብን ልጆቻችንን መርቀን ወደ ግንባር ልከናል ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ሰአዳ ያሲን ናቸው፡፡

ወይዘሮ ፈንታ ኢብራሂም በበኩላቸው ሀገር ከሌለ ህዝብ የለም የሕዝብ ሰላምና ደህንነት የሚጠበቀው ደግሞ በሰራዊታችን በመሆኑ እኛ ሴቶች አሸባሪው እስኪደመሰስ ድጋፋችን አይቋረጥም ብለዋል።