አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ኢትዮጵያን ሳይሰስት ያገለገለ ታላቅ የጥበብ ሰው

 ጷጉሜ 2/ 2013 (ኢዜአ) አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ኢትዮጵያን ሳይሰስት ያገለገለ ታላቅ የጥበብ ሰው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ አውድ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ደማቅ አሻራቸውን ካሳረፉ የኪነ ጥበብ ሰዎች መካከል ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ አንዱ ነበር፡፡

ታላቁ ሙዚቀኛ አለማየሁ 'ወርቃማው' ተብሎ ለሚጠራው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን የመጀመሪያው ተጠቃሽ ድምጻዊ እንደነበር  የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት ህልፈቱን አስመልክቶ ተናግሯል።

በ1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ አባ ኮራን ሰፈር ከአባቱ አቶ እሸቴ እና ከእናቱ ወይዘሮ በላይነሽ የሱፍ የተወለደው አለማየሁ እሸቴ ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ይናገራል።

የሮክኤንድ ሮል አቀንቃኙ ኤልቪስ ፕሪስሊ በአለማየሁ የሙዚቃ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረበት ይነገራል።

ከአማርኛ ውጭ የእንግሊዝኛ እና ሱዳንኛ ዘፈኖችን በተለያዩ የአለም አገራት በመዘዋወር በማቅረብ ተወዳጅነትን ማትረፉ እንዲሁ።

ድምጻዊው ከ400 በላይ ሙዚቃዎችን ሰርቶ ለአድማጭ አቅርቧል፡፡

ህልፈተ ህይወቱን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ ለታላቁ ድምጻዊ በመስቀል አደባባይ የመጨረሻ አሸኛኘት አድርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት" አለማየሁ ለአገሩ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን መስራቱንና ስራዎቹም ህያው እና ዘወትር ሲታወሱና ሲዘከሩ የሚኖሩ" ናቸው ሲሉም አክለዋል።

አለማየሁ እሸቴ አገሩን በታላቅ ቅንነትና ፍቅር በማገልገል ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ስራዎችን የሰራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

እለቱም ኢትዮጵያ ያገለገሏትን የምታከብርበት ቀን እንደመሆኑ አለማየሁ በቅንነት ለአገርህ ለሰራኸው ስራ እናመሰግናለን ብለዋል።

ለቤተሰቦቹሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለሙያ አጋሮቹ እንዲሁም በአገር ዉስጥና በመላው ዓለም ለሚገኙ አድናቂዎቹ በራሳቸውና በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በነዋሪዎች ስም ልባዊ መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

የባህል እና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው አለማየሁ እሸቴ በተሰጠው መክሊት ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን የሰራ ድምጻዊ ነው ብለዋል።

ጥበብና እውቀት የሰው ልጆች ቀዳሚ ሀብት መሆን እንዳለባቸው በሙዚቃዎቹ ማስተማር የቻለ የጥበብ ሰው እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን አስመልክቶ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ፣

"ሀገሩን አጥብቆ በመውደድና ለሀገሩ ከልብ በመሥራት ለብዙ ከያንያን አርአያ የሆነው ዓለማየሁ እሸቴ ማረፉን ሰምቼ እጅግ አዝኛለሁ። ሰሞኑን ወጣትና አንጋፋ ከያንያን ስለ ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ ሙዚቃ እንዲያወጡ ሲያስተባብር እንደነበር አውቃለሁ። ሥራዎቹ ኢትዮጵያን ከፍ እንዳደረጉ ይኖራሉ። ለኢትዮጵያ የሠራ ያርፋል እንጂ አይሞትም" ብለዋል፡፡

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከዋሊያስ፣ ከአይቤክስ፣ ከሸበሌ፣ ከዳህላክና ሮሃ ባንዶች ጋር አብሮ የሰራ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተቀጥሮ ለረጅም ጊዜ አገልግሏል።

አርቲስት አለማየሁ "ተማር ልጄ" እና "አዲስ አበባ ቤቴ" በሚሰኙት የሙዚቃ ስራዎቹ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል።

"የወይን ሃረጊቱ"፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፣ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ" ከመጀመሪያ ዘፈኖቹ መካከል መይጠቀሳሉ።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ የአራት ወንድና የሶስት ሴት ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፤ አራት የልጅ ልጆችን ለማየትም በቅቷል።

ሆኖም ነሐሴ 27 ቀን 2013 ባደረበት የልብ ሕመም በ80 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን በዛሬው እለት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ስርአተ ቀብሩ ተፈፅሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም