ቀጥታ፡

አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የአሽከርካሪ የሙያ ብቃት ፍቃድ በሚሰጡ ተቋማት ላይ እርምጃ ይወሰዳል -ባለስልጣኑ

አዳማ ጳጉሜ 2/2013 ( ኢዜአ) አሮጌ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የአሽከርካሪዎች የሙያ ብቃት ፍቃድ በሚሰጡ የማሰልጠኛ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስገነዘበ።
ባለስልጣኑ በክልሉ አሳሳቢ እየሆነ በመጣው የተሽከርካሪ አደጋ መንስኤና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ አካሄዷል።

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልቃድር ሁሴን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በሚደርሰው የተሽከርካሪ አደጋ መንስኤ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

የአሽከርካሪ የሙያ ብቃትና ስነ ምግባር የሚረጋገጠው በስልጠና ቆይታው በሚያገኘው ቴክኒካዊ እውቀትና ክህሎት መሆኑን ተናግረዋል ።

በክልሉ ከሚደርሰው የተሽከርካሪ  አደጋ 78 በመቶ የሚደርሰው በአሽከርካሪ የብቃት ማነስ መሆኑን አመልክተዋል።

ለችግሩ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች የማሰልጠኛ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመው  ከመስመር የወጡና አሮጌ ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው ስልጠና በሚሰጡት ላይ የማያደግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።

እስካሁን በሶስት ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተወሰደ እርምጃ  ፍቃዳቸው ተሰርዞ ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሉ አሽከርካሪዎችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙትና የተቀመጠውን ደረጃ ሙሉ በሙሉ አሟልተው ያልተገኙ ላይ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አመልክተዋል።

በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ  አደጋ ለመቀነስ የተቀናጀ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

" ከአሽከርካሪ-ተሽከርካሪና ከቁጥጥር አንፃር ህብረተሰቡ፣ የትራንስፖርት ዘርፉና የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ቦርድ በማቋቋም በትብብር እየሰራን ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

በባለስልጣኑ የትራፊክ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ለማ በበኩላቸው በክልሉ የአሽከርካሪ የሙያ ብቃት ስልጠና እየሰጡ ካሉ 214 ተቋማት ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት ደረጃቸውን ጠብቀው ከመስራት አንፃር ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል ።

ክፍተቱ ለታየባቸው ተቋማት የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በተሽከርካሪ አደጋ የሚደርስ የሰው ህይወት መጥፋት  መጠን ቢቀንስም አጠቃላይ የተሽከርካሪ  አደጋ መጨመሩን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ዘርፍ፣ ከማህበራትና ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በነበረውን ቅንጅት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በትራፊክ ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ላይ የተሻለ ስራ መሰራቱን አውስተዋል።

ባንጻሩ በበጀት አመቱ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ 226 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙንና በ135 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል ።

በዘርፉ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ፣ የራዳር፣ በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደረግ የአልኮል መጠን ልኬት ቴክኖሎጂና የማስጠንቀቂያ ቴክኖሎጂዎች በተያዘው 2014 የበጀት ዓመት በመንግስትና በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም