በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ሊብሶ ከተማ በአሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል

140

ጷጉሜ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ሊብሶ ከተማ በአሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባታል።

የኢዜአ ሪፖርተር በሊብሶ ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ የከተማዋ ቤቶች በሙሉ የበራቸው ቁልፍ እየተሰበረ ተዘርፏል፣ የቀረው ጥቅም እንዳይሰጥ ተደርጎ ወድሟል።

የሊብሶ ከተማ ነዋሪውና የ12ኛ ክፍል ተማሪው ወጣት መሀመድ ሰይድ ከትምህርት ጎን ለጎን በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ሽያጭ የሚተዳደር መሆኑን ይገልፃል።

የሽብር ቡድኑ በከተማዋ በቆየበት ጊዜ ሙሉ ንብረቱን ዘርፎ የሞተር ሳይክሉን ሰባብሮ፣ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዋ (ባጃጅ) ባለመቀሳቀሷ በቆመችበት ሲስተሙን አበላሽቶና ቆራርጦ ሂዷል ብሏል።

ሌላው ውሀን ጨምሮ የለስላሳ መጠጦችና የባጃጅ ስፔር ፖርት ማከፋፈያ መደብር ባለቤት የሆነው ወጣት አኑዋር ያሲን የፍሬን ዘይት፣ የሞተር ዘይትና ቸርኪዎች በሙሉ በአሸባሪው ተዘርፈውብኛል ብሏል።

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ቴሌቪዥንና ፍሪጅ ጨምሮ ሙሉ ንብረቱ ተዘርፏል፣ የቀረው ጥቅም እንዳይሰጥ ሆኖ እንደወደመበትም ተናግሯል።

የአካል ጉዳተኛ የሆነው ወጣት አብዱ አዲሱ ለዓመታት ለፍቶ ያቋቋመውንና ህይወቱን የሚመራበት አንድ ሱቁ ሙሉ በሙሉ በአኘባሪው ተዘርፎበታል።

ከዚህ በኋላ ለእኔ ህይወት አስቸጋሪ ነው፤ ተስፋየን ሁሉ አጨልሞብኛል በማለት በምሬት ገልጿል።

አሸባሪው ህወሃት ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ ንጹሀንን ገድሏል፣ ዘርፏል፣ ያልቻለውን በማውደም ታሪክ የማይረሳው ወንጀል ፈፅሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም