የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ከዚምባቡዌ አቻው ጋር ያደርጋል

176

ጷጉሜ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ካታር በታዝጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል።

እ.አ.አ በ2022 ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በሚደረገው የአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ባለፈው ሳምንት መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሰባት ከጋና፣ ዚምባቡዌና ደቡብ አፍሪካ ጋር በምድብ ሰባት ተደልድሏል።

ዋልያዎቹ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በአክራ ከጋናው አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከዚምባቡዌ አቻው ጋር ያደርጋል።

በክሮሺያዊው ዝድራቭኮ ሎጋሩቪች የሚመራው የተጋጣሚው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቱ ይታወቃል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች እስካሁን እርስ በእርስ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፋለች።

ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ ጨዋታቸውን ያደረጉት እ.አ.አ በ1988 በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር ሲሆን፤ ጨዋታውን ዚምባቡዌ 2 ለ 1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት ደረጃ 137ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ዚምባቡዌ  108ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ዛሬ የሚደረገውን ጨዋታ የሲሺየልሱ በርናንድ ካሚል በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ሁሉም ረዳት ዳኞች በተመሳሳይ ከሲሺየልስ ናቸው፤የጨዋታው ኮሚሽነር የኤርትራ ቹቹ ገብረመድህን የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነው ተመድበዋል።

ትናንት ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሰባት በተደረገው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ጋናን 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወቃል።ቃል።

በ10 ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የአፍሪካ(የካፍ) ዞን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከየምድቡ አንደኛ ሆነው የሚያልፉ 10 አገራት በሚወጣላቸው እጣ መሰረት እርስ በእርስ በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ድምር ውጤት የሚያሸንፉ አምስት አገራት ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2014 በብራዚል አስተናጋጅነት ለተካሄደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን ማጣሪያ የመጨረሻው ዙር ቢደርስም በናይጄሪያ አቻው በድምር ውጤት 4 ለ1 ተሸንፎ ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ሳይችል መቅረቱ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ2022 በሚካሄደው በኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ 32 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም