“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ሃሳብ የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

245

ጳጉሜ 2/2013(ኢዜአ) “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ሃሳብ የአሸባሪውን ህወሃት አገር የማፍረስ እቅድ ለማጋለጥ የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።

የወጣቶች ንቅናቄው “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ሃሳብ ከመስከረም 3 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዩዝ ኢንፓወርመንት ማኅበር እና አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ አስተባባሪ ዓለምአየሁ ሰይፉ፤ የወጣቶች ንቅናቄው በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመመከት መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳተ መልኩ የሚነዛው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት በንቅናቄው ይሰራል ብሏል።

“የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ-መንግስት” ዓለም አቀፍ የንቅናቄ የአስተባባሪ ኮሚቴው ምክትል ጸኃፊ አክሊሉ ታደሰ፤ በንቅናቄው ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ ብሏል።

የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ፣ የአሸባሪውን ህወሃት አገር የማፍረስ ወረራ ማጋለጥ፣ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ግፍ ማሳየት፣ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያውያን የተጠላ መሆኑን ማሳወቅ የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን ገልጿል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ወረዳዎችና እና ከተሞች የፖስታ ማሰባሰቢያ ጣቢያ ዝግጅት መደረጉም ታውቋል።

ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጠቀሜታ ይኖረዋል የተባለው “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ-መንግስት” የፖስታ መልዕክት ለአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እንዲደርስ ይሰራል ተብሏል።