ሰራተኞቹ ለሰራዊቱ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ አበረከቱ

289

ነገሌ ፤ ጷጉሜን 2/2013 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች  ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንዲውል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ አበረከቱ።

ሰራተኞቹ ገንዘቡን ለሰራዊቱ ማበርከታቸውን ይፋ የተደረገው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በነገሌ ከተማ በተወያዩበት ወቅት ነው።

በውይይት መድረኩ የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዲ ኩራ እንዳስታወቁት፤  ድጋፉን ያደረጉት 41 የጉጂ ዞን ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞችና አመራሮች ናቸው፡፡

ከወር ደመወዛቸው ተቆርጦ ለመከላከያ ሰራዊቱ እንዲሰጥ የወሰኑት አጠቃላይ  ገንዘብ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ  አመልክተዋል ።

መድረኩ ላይ የተገኙት የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ በበኩላቸው፤  ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ሽብርተኞችን የመመከት ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆብናል ብለዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የህግ ማስከበር ዘመቻ ከዞኑ ነዋሪዎችና ሰራተኞች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የዞኑ አርሶና  አርብቶ አደር ህዝብም  በርካታ ፍየሎችና ሰንጋ በሬዎች ማቅረቡንም አመልክተዋል፡፡

ሀገር ለማዳን በመንግስት የተላለፈውን ጥሪ በመቀበል የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል የተነሳሱ  በርካታ ወጣቶችም መሸኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ደስታ ብቸና በሰጡት አስተያየት፤ ሽብርተኞቹ ህወሀትና ሸኔ ሀገር ለማፍረስ  የሚፈጽሙትን የጥፋት ድርጊት ለመመከት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ 

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተግተው ሙያዊ አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን ሀገር የማዳን ጥሪውን በመቀበልም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሰራዊቱ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡