ሆስፒታሉ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ነጻ የህክምና አገልግሎት ዘመቻ ጀመረ

240

ዲላ፤ ጷጉሜን 1/2013 (ኢዜአ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት በዲላ ከተማ በዘመቻ መስጠት ጀመረ።

 አገልግሎቱ በጌዴኦ ዞን ሁሉም ወረዳዎች በመዘዋወር ይሰጣል።

በዘመቻው የመጀመሪያ ቀን በዲላ ከተማ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል።

የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ዶክተር ተስፋዬ ጉግሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሆስፒታሉ በዞኑ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ለመቆጣጠር አገልግሎቱን ይሰጣል።

ሆስፒታሉም ህብረተሰቡ ከተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዲጠበቅ ከመደበኛው በተጨማሪ አዲሱን ዓመት ምክንያት አገልግሎቱን ዘመቻ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ዘመቻው ምርመራ፣ የማማከርና የመድሃኒት አገልግሎትን  እንደሚያካትት ጠቅሰው፤ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በዘመቻው የመጀመሪያ ቀን ውሎ በዲላ ከተማ ለ500 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 200 በሚደርሱት የስኳርና የደም ግፊት ምልክት እንደሚታይባቸውና 27ቱ ለተጨማሪ ምርመራ መላካቸውን ዶክተር ተስፋዬ አስረድተዋል።

የምርመራ አገልግሎቱን በተሟላ መሳሪያዎችና ባለሙያዎች ታግዘው በነጻ  በማግኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አቶ ለማ ተፈራ ናቸው።

በባለሙያዎች የተሰጣቸውን ምክር በመጠቀም ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቀሚ ወይዘሮ ሮሃማ ወልደዮሐንስ፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራ የማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸውም በቸልተኝነት ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በምርመራው የደም ግፊት በሽታ ምልክት እንደታየባቸውና ለበሽታው አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች በመራቅ ጥንቃቄ አደርጋለሁ ብለዋል።

በጌዴኦ ዞን ስኳርና ደም ግፊትን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት በመስፋፋቱ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ መምጣቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።