የኤች አይቪ ኤድስ መድሃኒት የሚያቋርጡ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ቤት ለቤት የመድሃኒት እደላ ፕሮግራም ተጀመረ

82

ጎንደር፤ ጷጉሜን 01/2013 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኤች አይቪ ኤድስ መድሃኒት የሚያቋርጡ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚያግዝ የቤት ለቤት የመድሃኒት እደላ ፕሮግራም ተጀመረ።

የዞኑ ጤና መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና ቁጥጥር ፕሮግራም ያከናወናቸውን ተግባራትን ገምግሟል።

የመምሪያው የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና ቁጥጥር ኦፊሰር አቶ ደርበው ሙላው እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በዞኑ የኤች አይቪ ኤድስ መድሃኒት ከሚከታተሉ 5ሺ 100 ህሙማን መካከል 216 የሚሆኑት መድሃኒቱን አቋርጠዋል፡፡

ህሙማኑ መድሃኒቱን ለማቋረጥ የተገደዱት የኮሮና ወረርሺኝ በሽታ ባሳደረባቸው የጤና ስጋት ምክንያት በየወሩ ወደ ጤና ተቋማት ተመላልሰው ለመውሰድ ባለመቻላቸው ነው፡፡

የኤች አይቪ ኤድስ ታማሚዎች መድሃኒቱን በማቋረጣቸው ሳቢያ የሚደርስባቸውን ተጓዳኝ የጤና ችግርና ሞትን ለመቀነስ እንዲቻል በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የቤት ለቤት የመድሃኒት እደላ ፕሮግራም መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የመድሃኒት እደላ ፕሮግራሙ ለአንድ ታማሚ የስድስት ወር መድሃኒት በአንድ ጊዜ እንዲደርሰው በማድረግ በየወሩ ወደ ጤና ተቋማት የሚያደርገውን ምልልስና እንግልት በማስቀረት መድኃኒቱ የሚያቋርጡ ሰዎችንም ቁጥር መቀነስ ዓላማ ያደረገ ነው።

በዞኑ በኤች አይቪ ኤድስ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ምጣኔም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጨመሩን አቶ ደርበው ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተካሄደ ምርመራ 54 ሰዎች ላይ ቫይረሱ በደማቸው ሲገኝባቸው ይህም ከ2012 በጀት ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ20 ሰዎች ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ሰዎች ከ15 እስከ 25 ዓመት እድሜ ያላቸው ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁመው በሽታው አሁንም ወጣቶችን እያጠቃ መሆኑን በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የታች አርማጭሆ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና ቁጥጥር ኢፊሰር አቶ መለሰ ይሁን በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ መድሃኒት ሲወስዱ ከነበሩ 280 ህሙማን 34 ያህሉ በኮሮና ቫይረስ ስጋት አቋርጠዋል ነው ያሉት።

ችግሩን ለማቃለል በተደረገው ጥረት መድሃኒት ለሚያቋርጡ ህሙማን በወረዳው የቤት ለቤት መድሃኒት እደላ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከህክምናው ጎን ለጎን በተካሄደ ምርመራ በበጀት ዓመቱ ከ8ሺ በላይ ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 20ዎቹ ቫይረሱ በደማቸው እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል።

የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ጤና መኮንን ወይዘሮ ሰናይት ዋለልኝ እንዳሉት፤ በወረዳው ከ300 በላይ ቫይረሱ ላለባቸው ሰዎች ቤት ለቤት የመድሃኒት ማደል ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።

በግምገማው መድረክ ከዞኑ 15 ወረዳዎች የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎችና የዘርፉ አመራሮች መሳተፋቸውን ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም