የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበርን ንግድና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ የሁለቱ አገሮች የጋራ ኮሚሽን ገለጸ

242

ጳጉሜ 1/2013(ኢዜአ) የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበርን ንግድና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ የሁለቱ አገሮች የጋራ ኮሚሽን ገለጸ።

27ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎችና ኮሚሽነሮች ስብሰባ ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ በጅቡቲ አርታ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬዓለም ሽባባው ሁለቱ አገሮች የጋራ ራዕይና መዳረሻ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ለስትራቴጂክ አጋርነት መጠናከር የባለ ብዙ ዘርፎች የጋራ ትብብር መፍጠራቸውም ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ከንግድ ግንኙነት በዘለለ በሌሎችም ዘርፎች ላይ አጋርነት እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በበኩላቸው ስብሰባው በአገራቱ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ያጠናክራል ነው ያሉት።

የጅቡቲ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሰይድ ኑህ ሃሰን ደግሞ እንዲህ አይነት ውይይቶች አጋርነቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

በድንበሮች አካባቢ ያለውን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በተለይም ሕገ-ወጥ የሰዎችና የቁሳቁስ ዝውወርን ለመከላከል ያስችላልም ብለዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ምጣኔ ሃብታዊ ብቻ ሳይሆን በባህልና በማኅበራዊ ዘርፍም እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የድንበር ንግድና ደኅንነት፣ የሰዎችን ዝውውር፣ትራንስፖርት፣ ቀረጥ፣ የሰዎችና የእንስሳት ጤና ላይ ስብሰባው ትኩረት አድርጓል ተብሏል።

በድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር አስተማማኝ የሰውና የቁሳቁስ ዝውውር ለማሳለጥ እንደሚሰሩም ሁሉቱ አገሮች አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጠነከረ ወዳጅነትና አጋርነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብን በመጠቀም የንግድ ልውውጦችን ስታደርግ ጅቡቲ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመጠጥ ውሃን ከኢትዮጵያ እንደምታገኝ ይታወቃል።