"በምድር ላይ ብቸኛዋ የ13 ወር ፀጋ ባለቤት ሁሉን አብቃይ ኢትዮጵያ"

95

አዲስ አበባ፣ጷጉሜ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊነትን ቀን በሚመለከት በአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ አዘጋጅነት ቴአትር ቤቶች ያሰናዷቸውን የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች አቅርበዋል።

ባቀረቡት በመርሃ ግበሩ ላይ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የቢሮው ሃላፊ ፈይዛ መሀመድ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር፤ ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ቅኔ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በምድር ላይ ብቸኛዋ የ13 ወር ፀጋ ባለቤት፣ ሁሉን አብቃይና ምድረ ቀደምት ሲሉ ገልጸዋታል።

በመፅሐፍ ቅዱስ እና በቅዱስ ቁራአን ቀደምትነቷ የተነገረ፣ የሉሲ መገኛ፣ ከዳሉል እስከ ራስ ዳሸን ብዝሃ መልክዓ ምድርና አየር ፀባይ የታደለች ድንቅ አገር ሲሉም አብራርተዋል።

'ኢትዮጵያዊነት ሕብረ ቀለምነት ነው፣ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ' ብለዋል። 

ኢትዮጵያን ስንዘክር ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ ከልብ በመዋደድ መሆን አለበት ያሉት ሃላፊዋ "በህብረ ቀለም ያሸበረቀውን ኢትዮጵያዊነቴን ክብርና ሞገሴ፣ የማንነት መለያዬ" ነው፡፡ 

በኢትዮጵያዊነት ቀን ከያኒያን ኪነ ጥበብ የሚያቀርቡበት ብቻ ሳይሆን የኪነ ጥበብ መድረኮችንም በመታደም የሚያከብሩበት ነው ብለዋል። 

በየዓመቱ ጳጉሜን 1 ቀን የኢትዮጵያዊነት ቀን መከበሩንም ወይዘሮ ፈይዛ አድንቀዋል። 

'ለኢትዮጵያ ክብር እቆማለሁ፣ እዘምራለሁ' በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያዊነት ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ተዘክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም