በደቡብ ኦሞ በመኽር እርሻው ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል-አስተዳደሩ

451

ጂንካ ዻጉሜ 1/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን እስካሁን ባለው የመኽር ወቅት ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በሰብል ልማቱ 136 ሺህ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ በ2013/14 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 51 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። 

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ 40 ሺህ 600 ሄክታር መሬት  ታርሶ በበቆሎ፣በማሽላ፣በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቦሎቄና በሰሊጥ ሰብሎች ዘር ተሸፍኖ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ እስካሁን ከለማው መሬት ውስጥ 10 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች በመታገዝ  በኩታ ገጠም መዘራቱን ገልጸዋል። 

ቀሪው መሬት እስከ መስከረም 2014 ዓም አጋማሽ ድረስ ቶሎ በሚደርሱ የጥራጥሬ ሰብሎች ዘር  እንደሚሸፈን አቶ ታፈሰ አስታውቀዋል። 

ለመኽር እርሻው የሚያስፈልጉ የምርት ማሳደጊያ ግብአቶች መቅረባቸውን ጠቁመው አሁን ላይ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል እየቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

በደቡብ አሪ ወረዳ የአይዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታምሩ ማሲባይስ በሰጡት አስተያየት በአንድ ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳቸው ላይ  ከዘሩት  ስንዴ 70 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። 

ሶስት ሄክታር ማሳቸውን በትራክተር በማሳረስ ጤፍና አደንጓሬ ዘርተው እየተንከባከቡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የሼጲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማርቆስ አቻልቆ ናቸው።

ከሰብል ጎን ለጎን የጓሮ አትክልት እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ዘንድሮ የማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ፀረ አረም ኬሚካል አቅርቦት ችግር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል። 

በዞኑ እየተካሄደ ካለው የመኸር እርሻ ከዋና ዋና ሰብሎች ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።