ኢትዮጵያ በቱሪዝም ገበያ በዓለም ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል ቅንጅታዊ አሠራር ያስፈልጋል

63

አርባምንጭ፤ ጷጉሜን 1/ /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቱሪዝም ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግ ተመለከተ፡፡

ቱሪዝም ኢትዮጵያ በዘርፉ ልማት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ የጋራ ምክክር አካሄዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝም ፈንድ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ተክሉ እንዳሉት፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያ መዳረሻዎችን በማልማት፣ በማስተዋወቅና የቱሪዝም ፈንድን በማቋቋም ዘርፉ ለሀገራዊ ዕድገት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።

ሀገሪቱ በርካታ የመስህብ ስፍራ ቢኖራትም በተገቢው መንገድ ለምቶ ለህብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም እየሰጡ ባለመሆኑ የባለድርሻ አካላት ሚና ለማሳደግ የጋራ ምክክር መካሄዱን  ነው የገለጹት።

መዳረሻዎችን በማልማት ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ስራን በማስፋፋት ለባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ለማዋል የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሠራር አስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ሀገሪቱ የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ ምቹ የአየር ሁኔታና ሌሎችም የቱሪስት መስህቦች እንዳላት የተናገሩት ደግሞ በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝም ገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ወልደገብርኤል በርሄ ናቸው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ አመጣጥን ከሚገልጹ 17 ግኝቶች መካከል 13ቱ በኢትዮጵያ እንዲሁም ድንቅ የሆነውን የቡና ምርት ለዓለም ያበረከተች፣የአባይ ወንዝ መገኛና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ መሆኗ "ምድረ ቀደምት" ሊያሰኛት እንደቻለ አመላክተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማስቻል መዳረሻዎችን በማስተዋወቁ ረገድ ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩ ከተካፈሉት መካከል የዘመን ባንክ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አስራት ታደሰ በበኩላቸው፤መንግስትና የግሉ ባለሀብት በቱሪዝም ልማት ተቀናጅተው ባለመስራታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን እውቅናና ጥቅም ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል።

የቱሪስት መዳረሻዎች በማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ ሀገሪቱም ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ  ዘመን ባንክ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ ባለሀብቶች፣ ባንኮችና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም