ቢቢሲ ከሶሪያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በሰራው ዘጋቢ ፊልም ሃሰተኛ ዘገባ ማሰራጨቱን አመነ

179

ጳጉሜን 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) የእንግሊዙ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ከሶሪያ ጦርነት ጋር በተያያዘ “የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች በንጹሃን ላይ ተጠቅሟል” በሚል የሰራው ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) ሃሰተኛ መሆኑን አመነ።

ዴይሊሜይል በድረገጹ እንዳስነበበው ቢቢሲ “ራዲዮ 4” በሚል ፕሮግራሙ ላይ ያስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም በሃሰተኛ ማስረጃዎች የተሞላ እንደነበር የጣቢያው ቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ ተረጋግጧል።

እ.ኤ.አ በ2018 በሶሪያዋ ዶውማ ከተማ ተፈጽሟል የተባለው የኬሚካል ጥቃት ዘገባ አሌክስ በተባለና ራሱን የኬሚካል መሳሪያዎች ግልጋሎት ተከላካይ ድርጅት የቀድሞ ተቆጣጣሪ ያደረገ ግለሰብ የተወነበት ድራማ መሆኑን በምርመራው መረጋገጡ ተገልጿል።

በጣቢያው ክሎ ሃጂማቲው በተባለች የምርመራ ጋዜጠኛ ተሰርቷል የተባለው ዘጋቢ ፊልም የቢቢሲን ኤዲቶርያል መመሪያዎች ያላሟላና በሃሰተኛ ዘገባዎች የተሞላ እንደነበር በዘገባው ተመላክቷል።

የጣቢያው ቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ የቢቢሲ ዘገባ ስህተት ስለመሆኑ ግኝቱን ያቀረበው ዘገባው፤ አየር ላይ ከዋለ ከአስር ወራት በኋላ ባለፈው ሳምንት መሆኑን ተነግሯል።

በቅርቡ ጂኦ ፖለቲክስ ፕሬስ የተሰኘው ድረ ገጽ ምዕራባውያን ሶሪያን ለመበታተን “ባስማ” የሚል ፕሮጀክት መንደፋቸውንና በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ትላልቅ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንዲያሰራጩ ሲጠቀሙበት እንደነበር ማስነበቡ ይታወሳል።

ጂኦፖለቲክስ በዘገባው ተመሳሳይ ዘመቻ በኢትዮጵያ መከፈቱንም አስነብቧል።

እንደ ቢቢሲ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ሲኤንኤን ያሉ መገናኛ ብዙሃን የአሸባሪው ህወሃት የሳይበር ሰራዊት በመሆን ስልታዊ በሆነ መንገድ የአሸባሪውን ቡድን የተዛባ መረጃ ሲያሰራጩ መቆየታቸው ይታወቃል።

የቢቢሲ የምስራቅ አፍሪካ የትግርኛ ዘጋቢ የነበረው ደስታ ገብረመድህን ስራውን በመልቀቅ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን መቀላቀሉ የሚታወስ ሲሆን በሪፖርተርነት ሲሰራ በነበረበት ወቅት በሱዳን ስላሉት ስደተኞች በርካታ የተዛቡ ዘገባዎችን አሰራጭቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም