የተለየ ተስፋ የተቸረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት

72
           ሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካዋ አዲስ ሃገር ወደ ግጭት የገባችው ነፃነቷን ባወጀች ማግስት እኤአ በ2013 ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የቅቱን ምክትላቸውን ሬክ ማቻር የመንግስት ግልበጣ ለማካሄድ አሲሮብኛል የሚል ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግጭቶቹ እየሰፉ ሄደው ለበርካቶች ሞትና ስደት ምክንያት ከመሆናቸውም በላይ የደቡብ ሱዳን የተቃውሞ አሊያንስ በሚል ጥላ ስር በርካታ የተቃዋሚ ቡድኖች እንፈጠሩም ምክንያት ሆኗል። በነገራችን ላይ ይኸው የተቃዋሚ ጥምረት የቅርብ ጊዜው የካርቱሙ የሰላም ስምምነት አካል አልነበረም። የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት በነዳጅ ሃብት የበለፀገችዋን ሃገር ኢኮኖሚ ክፉኛ ከማሽመድመዱም በላይ በግብርና ምርቷ ላይ ሰፊ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። በያዝነው የፈረንጆቹ አመት ሰባት ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን (ከህዝብ ቁጥሩ ከግማሽ በላይ የሆነው) ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርጓል፡፡  እንደ አለም ባንክ መረጃ የሃገሪቷ 98 በመቶ ገቢ የሚገኝበት የነዳጅ ምርት በጦርነቱ ምክንያት ከነበረበት በቀን 350 ሺ በርሜል ወደ 120 ሺ በርሜል  አሽቆልቁሏል። በእርስ በእርስ ጦርነቱ እየረገፉ ለሚገኙት የደቡብ ሱዳን ዜጎች ለመድረስና  ወደ ተለያዩ ሃገራት የሚያደርጉትን ስደት ለመከላከል ከዚህ ቀደም ዘርፈ ብዙ የሰላም ጥረቶች ተደርገዋል። ፕሬዝዳንት ኪር እና ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ማቻር እኤአ በነሃሴ ወር 2015 የሰላም ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዓመቱ በሃምሌ ወር 2016 ዓ.ም  በዋና ከተማዋ ጁባ በተነሳ ግጭት ስምምነቱ ለፍሬ ሳይበቃ ቀርቷል። የካርቱሙ የሰላም ስምምነት ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሁለቱን ወገኖች በአዲስ አበባ ለማሸማገል ጥረት ካደረጉ በኋላ የተከናወነ ነው። በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲትና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ዶክተር ሬክ ማቻር መካከል በተደረሰው ስምምነት በሱዳኗ መዲና ካርቱም ተፈርሟል። በሰላም ስምምነቱ ወቅትም የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር እንዲሁም ዑጋንዳው አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቪኒ ተገኝተዋል። “ወንድሜ ሳልቫ ከግቦቻችን አንዱ… የተንኮታኮተውን የደቡብ ሱዳን ምጣኔ ሃብት ማዳን ነው።” ሲሉም የሱዳኑ ፕሬዝዳንት በሱዳን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል። የአሁኑ የሰላም ስምምነት በሃገሪቱ ላለፉት አምስት አመታት ተቀስቅሶ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን ለሚልቁት ደግሞ ለስደት የዳረገውን ግጭት ወደ ሰላም ለማምጣት ተስፋ ተደርጎበታል። “ዛሬ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሃገራችን የነበረውን ግጭትና ጦርነት መቋጫ” ያበጅለታል የሚል ተስፋቸውንም ገልጸዋል ፕሬዝዳንት ኪር። ዶክተር ማቻርም "የተኩስ አቁሙ ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን የሚካሄደውን ጦርነት መጨረሻ በማብሰር ለሃገሪቱ አዲስ ምዕራፍን ይከፍታል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ለሰብአዊ ዕርዳታ ለማድረግ የሚያስችል ኮሪደር መክፈትን፣ የጦርም ሆነ የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅ፣ የጦር ሃይልን ለህዝቡ ተፅዕኖ ከሚፈጥርባቸው ቦታዎች እንዲወጣ ማድረግ፤ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሃገሪቷን ለ36 ሳምንታት የሚያስተዳድር ጠንካራ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ስምምነት ከደረሱባቸው ጉዳዮች ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ስምምነቱ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የኢጋድ አባል ሃገራት የተለያዩ የሰላም ማስከበር ጥረቶችን እንዲሁም ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊነት የሚቆጣጠር ሃይል እንዲሰማራ እንዲያደርጉ የሚለውንም ያካትታል። ስምምነቱ በተለይ ከዚህ ቀደም "በተመሳሳይ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ከማቻር ጋር የምሰራ አይመስለኝም ብለው ይናገሩ የነበሩት ፕሬዚደንት ኪር የአቋም ለውጥ እንዳደረጉ ይቆጠራል" ሲል በደቡብ ሱዳን ላይ ትኩረቱን አድርጎ ጥናት የሚያካሄደው ካታም ሃውስ የጥናት ባለሙያ አህመድ ሶሊማን ተናግሯል። ለስልጣን ክፍፍል ይረዳ ዘንድ ሃገሪቷ ሶስት ዋና ከተሞች እንዲኖሯት የሚያደርግ አማራጭ በስምምነቱ ላይ የቀረበ ቢሆንም በተቃዋሚው ማቻር በኩል ጉዳዩ ውድቅ ተደርጓል። "ደቡብ ሱዳን አንድ ሃገር ናት፤ ስለሆነም ሶስት ዋና ከተሞች እንዲኖሯት የቀረበውን አማራጭ እንዲሁም የውጭ ሃይሎች ወደ ሀገራችን መግባታቸውንም እንዲሁ አልተስማማንበትም" በማለት የተቃዋሚ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጋራንግ ማቢዮር ተናግረዋል። የካርቱሙ የሰላም ስምምነት ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያውን ስምምነት ለመቋጨት ለቀጣይ ሁለት ሳምንት ቀጠሮ ተይዟል። ቀጣዩን ዙር የሰላም ስምምነት በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ለማካሄድ የታሰበ ሲሆን፤ የመጨረሻው የሰላም ውይይት ደግሞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። በየሰላም ድርድሮቹ ላይ ሁሉም ወገኖች በሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የቀረበውን ሃሳብም ይደግፉታል ተብሎም ተስፋ ተጥሏል። በሽግግሩ ወቅትም ሀገሪቱ ራሷን ለብሄራዊ ምርጫ ዝግጁ ታደርጋለች፤ ምርጫውን ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክፍት በማድረግ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ለስምምነት የቀረበው ሰነድ ያመለክታል። ሌላ ቅሬታ እንዳይፈጠር የሚያደርግ ሁሉንም የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ወገኖች ያካተተ ጥልቅ ሃገራዊ ስምምነት ሊደረግ ይገባል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይወተውታሉ። በኢጋድ የሰላም ስምምነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ተቃዋሚ ወገኖች ጨምሮ ከሰላም ሂደቱ ውጭ እስካሉት አካላት ተካተው በሰላም ሂደቱ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የፖለቲካ ተንታኙ አህመድ ሶሊማን የሚናገረው። በካርቱም በተካሄደው የሰላም ውይይት ወቅት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ምርታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ሃገራቱ እንዴት የነዳጅ ምርታቸውን በእጥፍ እንደሚያሳድጉ የገለፁት ነገር የለም። የተቃዋሚ ቡድኑ ቃል አቀባይ ከነዳጅ ምርቱ በፊት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ይቅደም በማለት ውጥኑን ቢቃወሙትም ካርቱም እና ጁባ ባለፈው ሰኔ ነበር በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙትን የነዳጅ አካባቢ መሰረተ ልማት በመጠገን ተጨማሪ የነዳጅ ምርት ለማውጣት ከስምምነት  የደረሱት። የነዳጅ ማውጫ አካባቢዎችንም ከሁለቱ ወገኖች በተውጣጣ የጦር ሃይል የመጠበቅ ስምምነትንም ሃገራቱ ከግምት አስገብተዋል። ይህም የቀጠናው ሠላምና ደህንነት ለኢኮኖሚ ትብብርና ትስስር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። የተፋላሚ ወገኖቹ የሰላም ስምምነት ለቀጣናው የሚኖረው ፋይዳ   ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ቁርሾ በኋላ ወደ ሰላም ስምምነት የመጡት ኢትዮዽያና ኤርትራ በአካባቢው የሰላም ድባብ እንዲሰፍን ያሳዩት ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ለሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች አወንታዊ ሚና ይኖረዋል። የሰላም አየር ርቆታል በሚባለው  የአፍሪካ ቀንድ የደቡብ ሱዳን ተቃራኒ ሀይሎች አለመግባታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ማሳየታቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ የሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የሰላም ድርድር ወደ ስኬት መምጣት በቅድሚያ ለሃገሪቱ ከዚያም ደግሞ ለአካባቢው ሃገራት ጠቀሜታው የጎላ ነው። ምክንያቱም የደቡብ ሱዳን ሰላም ሲናጋ ጎረቤቶቿ ማለትም ኢትዮዽያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ በሰላም ሊውሉና ሊያድሩ አችሉምና። የደቡብ ሱዳን ስደተኞችም በሁሉም በተጠቀሱት ሃገራት መገኘታቸው በሃገራቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ እያሳደረም ይገኛል። የሰላም ሂደቱ አዎንታዊ ውጤት በተለይ በሱዳን ላይ የሚኖረውን የተናጠል ፋይዳ ያየን እንደሆነም ሃገሪቱ አሁንም ከዚህ ቀደም የኤስ ፒ ኤል ኤ ቡድን አባላት ከነበሩ አማፅያን ጋር በውጊያ ላይ የምትገኝ መሆኗ እና ጦርነቱም በአካባቢዋ ካለው የሰላም እጦት ጋር ተያያዞ በቶሎ ሊቋጭ አለመቻሉ የሰላም ስምምነቱን ተፈላጊነት ያሳያል። በተጨማሪም ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር በመነጋገር የነዳጅ አጠቃቀሟን የማሳደግ አላማም ይዛለች፤ ይህንንም ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲቻል የሰላም ድርድሩ በውጤት መጠናቀቁ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ላለፉት አምስት አመታት በደቡብ ሱዳን የተካሄደው ጦርነት ያስከተለውን ሁኔታ በወጉ የሚረዱት የተቀሩት የአካባቢው ሃገራት የሰላም ስምምነቱ መልካም ነገርን ይዞላቸው እንደሚመጣ  አያጠራጥርም። ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በካርቱም የደረሱትን የተኩስ አቁም የሰላም ስምምነት እንደሚያከብሩት የመብት ተሟጋቾች  እምነት ጥለውባቸዋል። ከዚህ ቀደም ሁለቱ ወገኖች ከደረሱት ስምምነት የአሁኑ የተለየ መሆኑንም ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ተፋላሚ ወገኖቹ የደረሱትን ስምምነት በቀላሉ በመተላለፍ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ሱዳን በመለጠፍ መንግስትን የሚፋለሙበትን አማራጭ ያበጁ እንደነበርና በዚህ ስምምነት ግን አደራዳሪዋ ሃገር ራሷ ሱዳን በመሆኗ ጦር መሳሪያ ፍለጋ የሚሄዱበት አማራጭ ሊኖር እንደማይችል ያነሳሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኪር የተቃዋሚ ጥምረቱን አስመልክተው በየጊዜው የሚያስተላልፏቸው ያልተጠበቁ የአንድ ወገን ውሳኔዎች በተቃዋሚ አባላቱ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቁ ብሎም ተቀዋሚ ሃይሎቹ በፕሬዝዳንቱ ላይ እምነት እንዳይጥሉ  አድርጓቸዋል። በግጭቱ ሳቢያ የተሰደዱ የተወሰኑ ስደተኞች የሰላም ስምምነቱ እነዚህንም ወገኖች በማሳተፍ ተካሄዶ በሰላም ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ለመመለስ ተስፋን ሰንቀዋል። ምንም እንኳ ስደተኞቹ በሰላም ሂደቱ ላይ በደንብ ያልተገለፁ ጉዳዮች ከመኖራቸው ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ ቢያድርባቸውም በውጭና በሃገር ውስጥ በስደት እየተሰቃዩ ላሉ ወገኖቻቸው ፋታን ያመጣል በሚል በሰላም ስምምነቱ  ላይ ተስፋን ጥለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም