በኢትዮጵያ ላይ ጦር የከፈቱትን አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔን ለመደምሰስ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንሰለፋለን

86

በኢትዮጵያ ላይ ጦር የከፈቱትን አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔን ለመደምሰስ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንደሚሰለፉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ። አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በእጅ አዙር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙም ተጠይቋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሉዓላዊነት አደጋ ለመመከት ዓላማ ያደረገ ወቅታዊ ምክክር አካሂደዋል።

በምክክር መድረኩም ጥልቅ የውይይት ግምገማ በማካሄድ ከመግባባት ላይ መደረሱን የጋራ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ባወጣው የአቋም መግለጫ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በማክሸፍ ከመንግስት ጎን እንደሚሰለፉ አረጋግጠዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኮሙዩኒኬሽን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሮባሀ ሙርሃ፤ መንግስት በኢትዮጵያ የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት እያደረገ ያለውን ተጋድሎ በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ  ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በዚህም የእናት ጡት ነካሾቹን አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔ በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ የከፈቱት ጦርነት እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተዋደቀ ከሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከክልሎች ልዮ ኃይሎችና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ ለመዝመት ቁርጠኛ መሆናቸውን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ አንዳንድ ምዕራባውያን በእጅ አዙር በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያሉትን ጫና እና ተጽእኖ በጽኑ አውግዟል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የኢጋድ አባል አገራት  ሱዳንና ግብጽ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከሚዳፈር ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ግፊት እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ በአቋም መግለጫው አመልክቷል።

መንግስትም የዋጋ ንረትን ሚያባብሱትን፤ በኢትዮጵያ ላይ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ መገናኛ ብዙሃንና ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አመላክቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ በመግለጫውም ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ከጎኗ ለሆኑ አገራት መንግስታትና ረጂ ድርጅቶች ምስጋና አቅርቧል።

ኢትዮጵያዊያንም ጠላትን በመምታት አባቶቹን አኩሪ ገድል እየደገመ ከሚገኘው ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የአገራቸውን ዳር ድንበርና የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም