ለአሸባሪው ሸኔ ሊሰጥ የተዘጋጀ 25 ሺህ 335 የክላሽና ብሬን ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ

421

ነሐሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለአሸባሪው ሸኔ ሊሰጥ የተዘጋጀ 25 ሺህ 335 የክላሽና ብሬን ጥይት በጉዞ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአዲስ አበባ ከተማ በኮድ 3 A 32684 በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በድብቅ ተጭኖ ለአሸባሪው ሸኔ ሊሰጥ በጉዞ ላይ እያለ ነጆ ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በቁጥጥር ስር የዋለው 21 ሺህ 210 የክላሽ እና 4 ሺህ 125 የብሬን ጥይት መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ለአሸባሪው ሸኔ ለማድረስ በመጓጓዝ ላይ የነበረውን ጥይት በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው ክትትል የፌዴራልና የክልል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብር ኃይል የተቀናጀ ጥረት ማድረጋቸው ታውቋል።

በተጨማሪም አምቦ ባቢቻ የሚባል አካባቢ 3 ሺህ የክላሽ ጥይት ለአሸባሪው ሸኔ ለማድረስ የሞከሩ ግለሰቦች ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደባቸው ሲሆን በክትትሉ የህብረተሱቡ ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን በመጥቀስ ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል።

አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ አገር ለማተራመስና የሽብር ድርጊታቸውን ለመፈጸም በጋራ ለመስራት ስምምነታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ይሄው በብዙዎች ዘንድ “ያልተቀደሰ ጋብቻ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የአሸባሪዎቹ ስምምነት ኢትዮጵያን እንደሚያፈርስ በተደጋጋሚ ቃል የገባው አሸባሪው ህወሃት እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ ለመሸፋፈን አስቦ ያደረገው መሆኑን ነው የሚገልጹት።