ኢትዮጵያን በውትድርና ማገልገል ያንሳል እንጂ አይበዛም

89

ነሀሴ 30/2013 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያን በውትድርና ማገልገል ያንሳል እንጂ አይበዛም" ሲሉ የውትድርና ምሩቃን ገለጹ።

በአዋሽ አርባ የሚገኘው የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የመሰረታዊ ውትድርና የቡድን መሳሪያ ሰልጣኞችን እንዲሁም የቡድን መሳሪያ ምደብተኛ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን አስመርቋል። 

ከውትድርና ምሩቃን መካከል መሰረታዊ ወታደር ይትባረክ ታደሰ "በራሴ ፍላጎትና ሞራል ውትድርና የተቀላቀልኩት አገር አሳዛኝ ደረጃ ላይ መሆኗን በመመልከት ትምህርቴን አቋርጬ ነው" ይላል።

ሁሉም የሚሆነው አገር ሰላም ስትሆን ነው የሚለው ወታደሩ፤ ሌሎች ወጣቶችም "ኢትዮጵያን ወታደር ሆኖ ማገልገል ያንሳል እንጂ አይበዛም፤ ሌሎችም ይቀላቀሉን" ብሏል።

ሌሎቹ ምሩቃን የኋላው አበበ እና ታማኝሰው ምናለ፤ ወታደር የመሆን የቆየ ፍላጎት ስለነበራቸውና ህዝብ በሰላም ሰርቶ እንዳይኖር ብሎም ለአገር ሕልውና ሳንካ የሆነን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን "ጁንታም ሆነ ሌላ ወራሪ ሃይል እንዲደፍራት አንፈልግም" የሚሉት ምሩቃኑ፤ ሌሎች ወጣቶችም ውትድርና ሙያን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ላለፉት አስር ዓመታት በማዕከሉ ከቀላል እስከ ቡድን መሳሪያ አሰልጣኝነት በርካታ ወታደሮችን ያፈሩት ሀምሳ አለቃ መርዕድ ማረ በፍላጎታቸው ማዕከሉን የተቀላቀሉ ወታደሮች ጠላትን ለመደምሰስ የተሰጣቸውን ስልጠና በብቃት መወጣታቸውን ገልጸዋል።

በቡድን መሳሪያ የሰለጠኑት ወታደሮችም አሸባሪው ህወሃትን ሆነ ሌላ የውጭ ጠላትን ለመደምሰስ የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ስልጠናውንም በብቃት አጠናቀዋል ብለዋል።

የማሰልጠኛ ማዕከሉ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደጄኔ ጸጋዬ የጥፋት ሃይሉን ለአንዴና ለመጨረሻ ለመደምሰስ ከክልሎች የተውጣጡ ሰልጣኞች መሰረታዊ የአካል፣ የቴክኒክና የስነ-ልቦና ስልጠናቸውን በወኔና በብቃት በማጠናቀቃቸው "እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።

"ውትድርና አጥንት ከመከስከስና ደም ከማፍሰስ ባሻገር ውድ ሕይወት የሚሰጥበት በመሆኑ ዕድሉን ተጠቀሙበት" ብለዋል።

"የታሪካዊ ድል ባለቤት አካል በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል" ያሉት ኮሎኔል ደጀኔ፤ ሰልጣኞች ያገኙትን የንድፈ ሀሳብና የተግባር ዕውቀት በመጠቀም "አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ በአገር ሕልውና ዘመቻው ስኬታማ ግድጅ እንደምታከናውኑ እምነት አለኝ" ብለዋል"

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ በኩላቸው እንደገለጹት፤ የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ የፖሊስ አባላቱ መመረቅ ፖሊስ በሕልውና ዘመቻው እያደረገ ያለውን ተጋድሎ አቅም የሚያጎለብት ነው።

ምሩቃን ምልምል ወታደሮችና የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ ፖሊስ "ሰልጣኞች በሰለጠናችሁበት ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም በሚሰጣችሁ ግዳጅ ጠላትን ዳግም እንዳያንሰራራ መቅጣት ይገባችኋል" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በማንኛውም ውስጣዊና ውጫዊ ጠላት እንዳትደፈር መከታ መሆን እንዳለባቸውም ነው አደራ ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም