በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ኮቪድን እየተከላከሉ ለማስተማር ዝግጅት ተደርጓል

309

ነሀሴ 30/2013 (ኢዜአ) በ2014 የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ኮቪድን እየተከላከሉ ለማስተማር ዝግጅት ማድርጋቸውን ገለጹ።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

በመዲናዋ ተዘዋውሮ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ለመጭው የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ እያጠናቀቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የመድኃኒአለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደረጀ ከበደ፤ ትምህርት ቤቱ ለ2014 የትምህርት ዘመን አጠቃላይ የተማሪዎችን ድልድል ለመስራት ከሐምሌ 22 ጀምሮ ምዝገባ አካሂዷል።

የኮቪድ ፕሮቶኮልን  መሰረት በማድረግ ትምህርት ቤቱን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ ተሰርቷል ብለዋል።

የጋረ ጉሪ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ከድር ጃርሶ እና የጄኔራል ታደሰ ብሩ አንደኛ ደረጃ ቁጥር 1 ርዕሰ መምህር ዳባ ተረፈ ትምህርት ቤቶቻቸው በ2013 የትምህርት ዘመን ኮቪድን እየተከላከሉ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት መከተላቸውን ይናገራሉ።

በመጪው የትምህርት ዘመንም ይህንን ውጤት ለማስቀጠል  ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የማቪስ አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በቀለ ቶሌራ፤ ትምህርት ቤታቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት፤ ለ2014 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች ለኮቪድ 19 መከላከያና ሌሎች እንደ ደብተር፣ ቦርሳና የተማሪዎች ደንብ ልብስ ግዢ ሂደት እየተከናነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመምህራን የዝውውርና ሽግግር ስራዎች በቅርቡ ተጠናቀው በአመታዊ የትምህርት ጊዜ መርሃ ግብር መሰረት ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤት ማህበረሰቡን የኮቪድ 19 ክትባት መስጠት መጀመሩን ገልጸው ሁሉም እንዲከተብ አሳስበዋል።