ለውጭ ገበያ ከሚላክ ቡና ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው

89

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) በተያዘው የ2014 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከሚላክ ቡና ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን የቡና ልማቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት መስጠቱንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ የውጪ ምንዛሬ ገቢ አቅምን ለማሳደግ በመስኩ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እያገዘ መሆኑን ነው የገለጹት።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገሪቱ ለውጭ ካቀረበችው የቡና ምርት 10 በመቶ የሚሆነውን ያቀረበው 'ቀርጫንሼ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ' መሆኑን ገልጸው፤ ኩባንያው ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ሠራተኞቹን በማስተባበር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና በውጪ ምንዛሬ ግኝት የተሻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ በ2013 በጀት ዓመት ለውጪ ገበያ ከቀረበ ቡና 927 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በተያዘው በጀት አመት የቡና አቅርቦትን በማሳደግ ገቢውን ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በበኩላቸው የቡና ልማትና ገቢን ለማስፋፋት በቡና ኢንዱስትሪ የተሰማራ ባለሀብት በቡና ልማቱም እንዲሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ከዚህ አንጻር ቀርጫንሼ ኩባንያ ከቡና ንግድ ባለፈ በመስኩ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማትና በውጪ ምንዛሬ ግኝት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው" ብለዋል

በተያዘው ዓመት እንደሀገር 248 ሺህ ቶን የታጠበና ደረቅ ቡና ለውጪ ገበያ መላኩን የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ በመጪው ዓመት 280 ሺህ ቶን ቡና ለመላክ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀርጫንሼ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ እስራኤል ደገፋ በበኩላቸው ዘንድሮ በሀገር ውስጥና በውጪ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ቢገጥሟቸውም የተሻለ ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል።

ኩባንያው ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታቸውን አሳድገው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውንና ምርታማ የሆኑ የቡና ችግኞችን የማሰራጨት ሥራ መስራቱን ጠቁመዋል።

ኩባንያው በ2013 በጀት ዓመት ከአርሶ አደሩ የሚቀበለውን ቡና በማዘጋጀት 30 ሺህ ቶን የታጠበና ደረቅ ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከ85 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱንም ገልጸዋል። 

በድርጅቱ በዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም በማሳየታቸው 200 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው የወርቃ ቅርንጫፍ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ሀብቴ ኩባንያው በአካባቢው ካሉ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡና ተረክቦ ለገበያ ለማቅረብ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም