በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ "የግብፅና የሱዳን አካሄድ በሃይማኖትም በሥነ ምግባርም ፍፁም ተቀባይነት የለውም

89

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2013 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ "የግብፅ፣ የሱዳን መንግሥትንና የአረብ ሊግ ያላቸው አካሄድ ሃይማኖታዊና የሥነ ምግባር እሴቶችን የሚፃረር በመሆኑ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ሲሉ የእስልምና አስተምሮት መምህሩ ሼህ ሰዒድ አህመድ ሙስጠፋ ተናገሩ።

ሼህ ሰኢድ በአዲስ አበባ የአላቅሷ መስጅድ ኢማም እና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራርም ናቸው።

ሼህ ሰዒድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ላይ ያላቸው አቋም ሙሉ በሙሉ ጉድለት ያለበት እና የጋራ ሀብትን በፍትሃዊነት መጠቀም እንደሚገባ የሚያዘውን ኢስላማዊ መርህ የሚፃረር ነው።

ሁለቱ አገሮች ለዘመናት የአባይን ውሃ በብቸኝነት ሲጠቀሙ ቆይተው አሁንም እኛ እየጠጣን እናንተ ይጥማችሁ ማለታቸው በሃይማኖትም ሆነ በሥነ ምግባር ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል

ግብፅ እና ሱዳን ህዳሴ ግድን ለማስተጓጎል የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ አስተውለናል ያሉት ሼህ ሰዒድ ድርጊታቸው ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

"የአባይ ወንዝ ከአላህ በረከቶች አንዱ ነው፤ አገሮች ፈጣሪያቸውን በማመስገን በፍትሃዊነት መጠቀም ግድ ይላቸዋል" ብለዋል።

"የራስን ጥቅም ለማሳካት ሲባል ሌሎችን መጉዳት በአላህ ዘንድ በእጅጉ የተጠላ ተግባር ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሌሎችን ባለመጉዳት መጠቀም መሆኑ በኢትዮጵያ ዘንድ ግልጽ አቋም መኖሩን መንግስት በተደጋጋሚ ማስረዳቱንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ግብፅ እና ሱዳን ያልተገባ ስጋታቸውን ትተው የአፍሪካ ህብረት እያደረገ ያለውን ጥረት ተቀብለው ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

በግድቡ ጉዳይ የአረብ ሊግ ያሳየው አድሏዊነትም ተቀባይነት የሌለው እና ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን ገልፀዋል።

በግድቡ ላይ ያለው ጣልቃ ገብነት “የተሳሳተ እና ፍትሃዊነት የጎደለው” ነው ያሉት ሼህ ሰዒድ የውሃ ሃብቱ ፍትሃዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው የአረብ ሊግ ገንቢ ሚና መያዝ አለበት ነው ያሉት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አጠቃላይ ክንውን ከ80 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም