ለጭሮ ወረዳ መንግስት ሰራተኞች መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና እየተሰጠ ነው

74

ጭሮ ነሐሴ 30/2013 (ኢዜአ)ሀገር ለማፍረስ የሚሞክሩ ሃይሎችን መመከት የሚችል ዜጋ መፍጠርን አላማ ያደረገ የመሰረታዊ ውትድርና ስልጠና በምዐራብ ሀረርጌ ዞን ለጭሮ ወረዳ መንግስት ሰራተኞች እየተሰጠ ነው ።

 የመንግስት ሰራተኛው መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና መውሰዱ ወታደራዊ መዋቅር ያለውና ሀገር ለማፍረስ ለሚመጡ ሀይሎች የማይንበረከክ ዜጋ ለመፍጠር እንደሚረዳ ተነግሯል፡፡ 

ወታራዊ መዋቅር ያለው ህብረተሰብ ከተፈጠረ ለፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል ።

ስልጠናው የመንግስት ሰራተኛው የህዝብ አገልጋይነቱን ሚና በመሪነት እንዲያከናውን እንዲሁም  ታማኝና ቀልጣፋ እንዲሆን  እንደሚያግዘው ተመላክቷል፡፡

የጭሮ ወረዳ ፖሊስ ምክትል ዳይሬክተር ዋና ሳጅን ግርማ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት  የስልጠናው አላማ የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ በሙሉ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስዶ አካባቢውንና ሀገሩን ነቅቶ የመጠበቅ አቅም እንዲኖረው ማስቻል ነው፡፡

አያይዘውም የውትድርና ስልጠናን ለህብረተሰብ በመስጠት የውጭ አጥቂን መከላከልና በራስ የመተማመን አቅሙ የዳበረ ሀገር ወዳድ ዜጋን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል ።

የወረዳው ፖሊስና የፀጥታ አካላት ከ5ተኛ ልዩ ሃይል ጋር በጋራ በመሆን ስልጠናውን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው ስልጠናው ለ15 ቀን እንደሚሰጥ አመልክተዋል ።

የጭሮ ወረዳ የፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ በበኩላቸው "ሀገራችን ጠላቷን እንድትመክት ደህንነቷን የሚያስከብርላት ሀይል ያስፈልጋታል" ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኛው ስራውን እየሰራ ራሱን፣ አካባቢውንና ሀገሩን የመጠበቅ ኃላፊነቱን  ከመወጣት ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ አርዓያ እንዲሆን ለማስቻል ስልጠናው እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

 "ሀገር ተደፍራ እጅና እግር አጣጥፎ የመቀመጥ ታሪክ ስለሌለን ራሳችንንና ሀገራችንን ለማዳን የሚረዳንን ስልጠና እየወሰድን ነው "ያሉት  ደግሞ መሰረታዊ ውትድርና እየተሰጣቸው ካሉ መካከል የጭሮ ወረዳ የፋይናንስ ሂሳብ ሰራተኛ ወይዘሮ  አበበ ናቸው።

ወይዘሮ ሰላማዊት አክለው ልጆቻችንን ልከን እኛ ወደ ኋላ አንቀርም ወደ ፊት እንቀጥላለን አሸባሪዎችን እንደመስሳለን" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም