ለህልውና ዘመቻውና ለተፈናቀሉ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሰንጋዎችና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደሴ ነሀሴ 30/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በህልውና ዘመቻው እየተፋለሙ ለሚገኙ የፀጥታ አባላትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሰንጋዎችንና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ተወላጆችን በመወከል ዛሬ ድጋፉን ያስረከቡት አቶ ይሁኔ ማዘንጊያ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ጥፋት በጋራ መከላከልና መመከት የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ ነው።

በድጋፉ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆችን በማስተባበር ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሰንጋዎችና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ድጋፉም 40 ሰንጋዎች፣ 260 ኩንታል ዱቄትና 1 ሺህ ብርድ ልብስ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለሠራዊቱ እንዲደርስ ሰንጋዎቹን ለደቡብ ጎንደር ዞን፤ ቁሳቁሱን ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን በኩል ለተፈናቃዮች ለማድረስ ዛሬ ርክክብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የክፋት ሁሉ ማሳያና የጭካኔ ባለቤት የሆነው አሸባሪ ህወሓት ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ይሁኔ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ እንዳሉት፣ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ተፈናቅለው ደሴ፣ ኮምቦልቻና አካባቢዋ የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከ223 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡

መንግስት ህዝብና ተቋማትን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ሁሉም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ዛሬ ያደረጉት ድጋፍ የሚመሰገንና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አቶ መሳይ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም