በህልውና ዘመቻው በሙያችን ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ­- የህክምና ሳይንስ ተመራቂዎች

96

ደብረብርሃን፣ ነሐሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት ለመመከት እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ በሙያቸው ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ተመራቂ ገለፁ።

ዩኒቨርሲቲው በህክምና ሳይንስ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 158 የጤና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል። 

በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በ2ኛ ዲግሪ የተመረቁት አቶ ሳሙኤል ሲሳይ ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ በውጭ ሃይሎችና በአሸባሪው የህወሃት የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከመከላከያ ጎን በመሆን በሰለጠኑበት ሙያ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በነርሲንግ ሙያ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀችው ቤተልሄም ዘበነ በበኩሏ በባህሪው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትለውን ጦርነት ለመመከት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግራለች።

''በአሸባሪው ህወሃት የተቃጣብንን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለመመከት የሚዋደቁ የሰራዊት አባላትን በስፍራው ተገኝቼ በሙያዬ ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ'' ብላለች።

"በዚህ አስቸጋሪና ሀገር አደጋ ላይ በወደቀችበት ወቅት በጤና ሙያ ዘርፍ በግንባር ከሚዋጋው ሰራዊት ባልተናነሰ እገዛ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሀገራዊ ግዴታዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ" ስትል ተናግራለች።

የዩኒቨርሲቲው አስራት ወልደየስ ጤና ሳይንስ ካምፓስ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ቴዎድሮስ ክፍለዮሃንስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት “ተመራቂ ተማሪዎች የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ ከመንግስት ጎን ሊቆሙ ይገባል” ብለዋል።

"አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የጤና ሙያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊ በመሆኑ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ግንባር ቀደም ሆነው ለማገልገል መዘጋጀት አለባቸው" ሲሉ አስገንዝበዋል።

"በህወሃት ፅንፈኛ ቡድን እየተፈፀመ ያለው ጥቃት በውጭ ጠላት ያልተደረገ አሳፋሪ ተግባር ነው" ያሉት ደግሞ የእለቱ ክብር እንግዳና የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ናቸው፡፡

ሀገር ለማዳን የተጀመረው የህልውና ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ በሁሉም መስክ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተመራቂ የጤና ባለሞያዎች ግንባር ድረስ በመሄድ በማገልገል አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በህብረተሰብ ጤና አገልግሎት፣ በህክምና፣ ቤተ-ሙከራ ጨምሮ በ11 የትምህርት ዓይነቶች ከተመረቁ 158 ባለሞያዎች መካከል 84ቱ ሴቶች ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም